ሱፐር ስፖርት ለሊጉ ክለቦች የሰጠው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች ለተወጣጡ አመራሮች የተሰጠው የሁለት ቀን ስልጠና ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የምስል እና የስያሜ መብት የገዛው ሱፐር ስፖርት ከመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮብ ማኅበር ጋር በመተባበር የሊጉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ለክለብ ፕሬዝዳንቶች እና ሥራ-አስኪያጆች ስልጠና ሊሰጥ እንደነበር ከትናንት በስትያ ገልፀን ነበር። በደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ከትናንት ጀምሮ መሰጠት የጀመረው ይህ ስልጠናም ዛሬ ፍፃሜውን ማግኘቱ ታውቋል።

በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል የተሰጠው ስልጠና በዋናነት ስለብራንዲንግ፣ ስለ ስፖንሰር ሺፕ መርሆች እና ስለ አጠቃላይ ህጋዊ ስምምነቶች ሀሳብ እንደተነሳበት ተገልጿል። በተለይ ሊጉ በቴሌቪዥን ስለሚታይ ከሌሎቹ ሀገራት ሊጎች ጋር እንዴት ደረጃውን ማስተካከል አለበት፣ የተጫዋቾች የዝውውር ስምምነት ምን መምሰል አለበት፣ የጨዋታ ቀን ዝግጅቶች እንዴት መሆን አለባቸው፣ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ምን ዝርዝሮች ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም ክለቦች የመረጃ ክፍተቶችን እንዴት መዝጋት አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ሀሳቦች እንደተነሱ ለማወቅ ችለናል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚር ፍራንሱዋ እና የሱፐር ስፖርት የኢትዮጵያ ተወካይ ወ/ሮ ሰሎሜ የተገኙበትን ስልጠና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ስመ ጥር ባለሙያዎች በበይነ-መረብ የሰጡ ሲሆን በቀጣይም ከሊጉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው የተለያዩ አካላትም እንደሚሰጥ የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፈ ነግረውናል።