የሉሲዎቹ ወርሀዊ ደረጃ ይፋ ሆኗል

ፊፋ የዓለም የሴት ብሔራዊ ቡድኖችን ወርሀዊ ደረጃ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ሲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ባለበት ደረጃ ተቀምጧል።

በየወሩ የሀገራትን የእግርኳስ ደረጃ የሚያወጣው ፊፋ ከቀናት በፊት የወንድ ብሔራዊ ቡድኖችን ደረጃ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ከሳምንት በፊት በወጣው ደረጃም ዋልያው 137ኛ ደረጃን መያዙ ይፋ ሲሆን አሁን ደግሞ የሉሲዎቹ ደረጃ ተገልጿል። በዚህም 168 የሴት ብሔራዊ ቡድኖች በዝርዝሩ በተካተቱበት ደረጃ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዓለም 112ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 15ኛ ደረጃን መያዙ ተመላክቷል። በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ወር ምንም ጨዋታ ባያደርግም መውረድ እና መውጣት ሳያሳይ በ1151 ነጥቦች ባለበት ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ከዓለም 38ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ናይጄሪያ የአህጉሩን ደረጃ በበላይነት ስትመራ ካሜሩን እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ተከታዮቹን የአፍሪካ ደረጃ ይዘው ተቀምጠዋል።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነሀስ ሜዳሊያ ያገኘው የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሁንም የዓለም ቁንጮ መሆኑን ቀጥሏል። በዚሁ ውድድር የብር ሜዳሊያ ያገኘው የሲውድን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ሦስት ደረጃዎችን በማሻሻል ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። አንድ ደረጃ የተንሸራተተው ጀርመን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ፊፋ ባወጣው መረጃ መሠረት ባሳለፍነው ወር ከፍተኛ የነጥብ መሻሻል ያስመዘገበችው ሀገር ሲውድን (+78.20) ስትሆን ከፍተኛ ደረጃን ያሻሻለችው ደግሞ ዛምቢያ (+10) መሆኗ ተመላክቷል።