የኢትዮጵያ ቡና እና ዩ አር ኤ ጨዋታን የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

መስከረም ሁለት ዩጋንዳ ላይ በዩ አር ኤ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የሚደረገውን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ተለይተዋል።

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፉን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ የምድብ ፍልሚያ ውስጥ ለመካፈል የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ እንዳለበት ይታወቃል። በዚህም ቡድኑ በመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከዩጋንዳው ዩ አር ኤ ጋር እንዲጫወት መርሐ-ግብር የተያዘለት ሲሆን ጨዋታዎቹንም መስከረም 2 እና 9 ኢንቴቤ እና ባህር ዳር (በቅደም ትከተል) ላይ ያከናውናል።

የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ ጨዋታ ዩጋንዳ ላይ ሲከናወንም ፍልሚያውን የሚመሩ ዳኞች ተለይተዋል። በዚህም ታንዛኒያዊው የመሐል ዳኛ ኤሊ ዓሊ ሳሲ በተመሳሳይ ከሀገራቸው ከመጡት ሳሊም ምኮንኮ መሐመድ፣ ሴፍ ምፓንጋ ካሲም ሴፍ እንዲሁም ማርቲን ኢሊፋስ ሳንያ ጋር በመሆን ጨዋታውን እንደሚመሩ ተገልጿል። መስከረም ሁለት የሚደረገውን ጨዋታ ከሩዋንዳ የተመረጡት ሚኬል ጋሲንግዋ በኮሚሽነርነት የሚመሩት ይሆናል።