ሀበሻ ቢራ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አዲስ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ሊያደርግ ነው

የኢትዮጵያ ቡና አጋር ሆኖ የዘለቀው ሀበሻ ቢራ ለተጨማሪ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የስፖንሰር ስምምነት በቅርቡ ሊፈፅም ነው።

ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ወደ እግርኳሱ ብቅ ያለው ሀበሻ ቢራ ከ2004 ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡናን በየዓመቱ በሚታደስ ስምምነት በተለያዩ መንገዶች ስፖንሰር በማድረግ መቆየቱ ይታወቃል። ባሳለፍነው ዓመት ለአንድ ዓመት ውሉን በማራዘም በነበረው ስምምነት በአጠቃላይ 28.25 ሚሊየን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ቡና ስፖንሰር ማድረጉ ሲታወቅ ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከአስር ዓመት በኋላ የአፍሪካ ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ተከትሎም ከፍተኛ የሆነ ሽልማት ለተጫዋቾቹ ማበርከቱ ይታወሳል።

አሁን ደግሞ በዓይነቱ ከፍ ያለ የተለያዩ ዝርዝር ስምምነቶች ያሉበት ለአምስት ዓመት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት የፊታችን ቅዳሜ በአራት ሰዓት ቦሌ ኤድና ሞል አካባቢ በሚገኘው ቤስት ዌስተርን ሆቴል በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።