ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከባድ ፈተና ለፍፃሜ ደርሷል

ከባድ ፍልሚያ ባስተናገደው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ንግድ ባንክ የዩጋንዳውን ሌዲ ዶቭን በመለያያ ምቶች 5-3 በመርታት ለዋንጫ አልፏል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዛሬው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ትዕግስት ኃይሌ ፣ ንግስት መዓዛ ፣ ሕይወት ደንጊሶ፣ ዓለምነሽ ገረመው እና ፀጋነሽ ወራናን በማሳረፍ በምትካቸው ታሪኳ በርገና ፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል ፣ ብዙዓየሁ ታደሰ፣ ሰናይት ቦጋለ እና አረጋሽ ካልሳን ወደ አሰላለፍ አምጥተዋል።

ጥሩ ፉክክር በተስተዋለበት በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ጅማሮ በመዲና ዐወል ሙከራ በማድረግ የጀመሩት ንግድ ባንኮች በግብ የተንበሸበሹበትን አጋማሽ ባያሳልፉም ከተጋጣሚያቸው የተሻለ አስፈሪነት ነበራቸው። 8ኛው ደቂቃ ላይ የመዲና እና ሎዛ አበራ ድንቅ ጥምረት ዳግም በታየበት አንድ ሁለት ቅብብል ሎዛ አክርራ በመምታት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ከመረብ ባረፈ ኳስ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች። ሊዲ ዶቮች ጥሩ ስትንቀሳቀስ በነበረችው ፋዚላ ኢኩዋፑት አማካይነት 10ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ምላሽ ለመስጠት አድረግው በታሪኳ በርገና ተመልሶባቸዋል። ኢኩዋፑት 20ኛው ደቂቃ ላይ ሌላም የግብ ሙከራ ከርቀት ማድረግ ችላ ነበር።

ዩጋንዳዊያኑ የንግድ ባንክ የኳስ ፍሰት ወደ አደገኛ ሙከራዎች እንዳይቀየር ጥሩ ጥረት አድርገው በታዩባቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች አልፎ አልፎ ከቆሙ ኳሶች እና ከርቀት ነበር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት። ግብ አስቆጣሪዋ ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጪ ካደረገችው የ18ኛ ደቂቃ ሙከራ በኋላ ንግድ ባንኮች ኳስ ይዘው ከግብ ክልላቸው በመውጣት እና የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ በመገደቡ ረገድ እምብዛም አልተቸገሩም። በማጥቃቱ በኩል ግን የሌዲ ዶቮችን ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት እንደልባቸው አልፈው መግባት እና ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ንግድ ባንኮች በተሻለ ንቃት ጫን ብለው በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መንቀሳቀስ ችለዋል። ያም ቢሆን እንደመጀመሪያው ሁሉ ግብ ጠባቂዋ ናካሪዞ ዴዚን ማስጨነቅ አልቻሉም። ይልቁኑም ሌዲ ዶቮች 62ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት ፋዚላ ኢኩዋፑት አክርራ በመምታት በማስቆጠሯ አቻ መሆን ችለዋል። ከግቡ በኋላ ብርቱካን ገብረክርስቶስን እና አለምነሽ ገረመውን ቀይረው ያስገቡት ንግድ ባንኮች አለመረጋጋት ቢታይባቸውም በቶሎ ወደ ቀደመ ብልጫቸው ተመልሰው ከፍ ያለ ጫና ፈጥረዋል። ሎዛ እና ሰናይት ቦጋለ ያደርጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂዋ ጥረት ሲድኑ በተለይም አረጋሽ ካልሳ 82ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠረችውን ያለቀለት የግብ ዕድል አስቆጠረች ሲባል ግብ ጠባቂዋ ናካሪዞ ዴዚን አድናባታለች። ተደጋጋሚ ሙከራ የተደረገባቸው ዩጋንዳዊያኑም በበኩላቸው ቀጥተኛ አጨዋወትን በመምረጥ አሉፓ አሉፖ እና ኖራ ጆዌሊያ ናጋዲያ ከባድ ሙከራዎችን አድርገው ነበር።

በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጥሩ ቅብብሎችን በመከወን ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ወደፊት ወርውረዋል። ያም ሆኖ ዩጋንዳዊያኑ ከፊት ሁለት ተጫዋቾችን በመተው ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ተስተውለዋል። ለግብ በቀረበው የኢትዮጵያዊያኑ የመጨረሻ የ90ኛ ደቂቃ ሙከራ መዲና ዐወል በቀኝ በኩል አድልታ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ግብ የላከችው ኳስ ለጥቂት በጎን በኩል የወጣ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ወደ ጭማሪ ደቂቃ አምርቷል።

በጭማሪ ደቂቃዎቹ ቀዳሚ አጋማሽ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ልጆች የ90 ደቂቃው ማብቂያ ላይ ወደነበሩበት ብልጫ ለመመለስ የተወሰኑ ደቂቃዎች ወስዶባቸዋል። በሂደት ወደ ግብ መቅረብ ቢጀምሩም ሌዲ ዶቮች ኳሶችን በረጅሙ በማራቅ የሚቃጣባቸውን ጥቃት ፍሬ አልባ አድርገውታል። 99ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የአጋማሹ አስደንጋጭ አጋጣሚ ቢሆንም ጥሩ ጨዋታ ያሳለፈችው የዩጋንዳዊያኑ ግብ ጠባቂ አድናባታለች። ሁለተኛውም 15ም ከሎዛ አበራ ኢላማውን ያልጠበቀ ጥሩ የቅጣት ምት ሙከራው ውጪ የንግድ ባንኮች የማጥቃት ትግል እና የሌዲ ዶቮች እልህ አስጨራሽ መከላከል ታይቶበት ያለግብ በመጠናቀቁ ተጋጣሚዎቹ በፍፁም ቅጣት ምት የመለያየታቸው ነገር የግድ ሆኗል።

በመለያ ፍፁም ቅጣት ምቶቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አምስቱንም ሲያስቆጥሩ ሌዲ ዶቮች አንድ በመሳታቸው ነጭ እና ጥቁር ለባሾቹ ከብርቱ ትግል በኋላ ለፍፃሜ ማለፋቸው ዕውን ሆኗል።

በፍፃሜው የኬንያው ቪሂጋ ክዊንስን የሚገጥመው ንግድ ባንክ አሸንፎ ዋንጫውን ካነሳ በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ተሳታፊ ይሆናል። ንግድ ባንክ በፍፃሜው የሚገጥመው ቪሂጋ ክዊንስን ከዚህ ቀደም በምድብ የመክፈቻ ጨዋታ 4-2 ማሸነፉ ይታወሳል።