የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል

በባቱ ከተማ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ከየኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፎ ያደረገው አርባምንጭ ከተማ አሸናፊ ሆኗል።

ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በአስራ ስድስት የከተማ እና የክልል ቡድኖች መካከል ከነሐሴ 16 ጀምሮ በባቱ ከተማ ሲካሄድ የቀ ዛሬ በደማቅ ሁኔታ ፍፃኔውን አግኝቷል።

ሦስት ሰዓት በጀመረው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በሀዋሳ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን በማሳረፍ ከዚህ ቀደም በመጀመርያው አስተላለፍ ያልገቡ ተጫዋቾችን ተጠቅሟል። በዚህም ዛሬ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የገባው ዮሐንስ ሙራድ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለት ኳስ ሮጦ በመግባት የግቡ ቋሚ የመለሰው በቡና በኩል የተደረገ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነው። በጥሩ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ቢጀምሩም ቡናዎች ከግብጠባቂ አንስተው ኳሱን መስርተው ለመጫወት አስበው በፈጠሩት ስህተት የተገኘውን ኳስ አማኑኤል ሞገስ በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀይሮ ሀዋሳዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በሚያደርጉት ቅብብሎሽ የሚፈጠሩ ስህህተቶችን በንቃት የሚጠብቁት ሀዋሳዎች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ መሬት ለመሬት በመምታት አማኑኤል ሞገስ ለቡድኑን ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጠንካራ ስብስባቸውን ይዘው የገቡት ቡናዎች ብልጫ ወስደው መጫወት ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ባለመቸላቸው አስቀድሞ በተቆጠረባቸው ሁለት ጎሎች ተሸናፊ ሲሆኑ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማ ውማሸነፉን ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

በመቀጠል በተካሄደው የአዳማ ከተማ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በመለያ ምት አርባምንጭ ከተማ አሸናፊ ሆኗል። የዕለቱ የክብር እንግዳ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከተጫዋቾች ጋር ባስጀመሩት ይህ የፍፃሜ ጨዋታ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዮትን ኮሚሽነር ተስፋዬን በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት አስቧል። በሁለቱም ቡድኖች በዛሬው ጨዋታ በተወሰነ መልኩ ተዳክመው የቀረቡ መሆናቸውን ብንመለከትም በአንፃራዊነት አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበር። የውድድሩ ኮከብ አጥቂ ሆኖ የተሸለመው ዮሴፍ ታረቀኝ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ የፍፃሜ ጨዋታን ያህል ተደጋጋሚ በሁለተም በኩል የጎል ሙከራዎችን አልተመለከትንም።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ከዕረፍት መልስ የተሻ የማጥቃት መንገዶችን አስመልክቶናል። በአርባምንጭ በኩል ቤዛ አበበ ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ ውጭ የመታው ኳስ የአዳማው ግብጠባቂ እንደምንም ያዳነበት ሙከራ ተጠቃሽ ነው። ከዚህ የአርባምንጭ ጠንካራ ሙከራ በኃላ በቀሩት ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች ዮሴፍ ታረቀኝ የተሻገረለትን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ በቮላ የመታው ለጥቂት በግቡ አናት ላይ የወጣው ለአዳማ የሚያስቀጭ አጋጣሚ ነው። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር አርባምንጮች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ተገድበው መከላከል ላይ ማተኮራቸው እነርሱን አስከፍተው ጎል ለማስቆጠር አዳማዎች ጥረት ቢያደርጉም የአርባምንጭን ጠንካራ መከላከል ጥሰው ጎል ማስቆጠር አቅቷቸው ጨዋታው ያለ ጎል በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቷል።

በመለያ ምቱም የውድድሩ ምርጡ ግብጠባቂ የአርባምንጩ ሠራዊት አራቱን የአዳማን የመለያ ምት በማዳን አስደናቂ የሆነ ብቃቱን በመሳየት አርባምንጭ ከተማ 2–0 በማሸነፍ የውድድሩን ዋንጫ አንስቷል።

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች ውድድር የተሳተፈው አርባምንጭ ከተማ ባለ ድል በመሆን በዕለቱ የክብር እንግዳ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል።

ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ፌዴሬሽኑ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በስኬት በተጠናቀቀው በዚህ ውድድር የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳሬክተር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ከሌሎች ሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ላደረጉት የላቀ አስተዋፆኦ ሊመሰገኑ ይገባል። በመጨረሻም እንደነዚህ ያሉ መሰል ውድድሮች በቀጣይ ያልተካፈሉ ክልሎች እና ክለቦችን አስገዳጅ ህጎችን በማውጣት የሚሳተፉበትን መንገድ በመፈለግ በቀጣይነት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲዘጋጅ መልዕክታችን ነው።


* የኮከብ ተሸላሚዎች ዝርዝር
– ኮከብ ተጫዋች – ሰይፈዲን ረሺድ (አዳማ ከተማ)

– ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – ሙሉቀን በቀለ (በ7 ጎል -አዲስ አበባ ከተማ)

– ኮከብ አሰልጣኝ – አዱኛ ገላነህ (አርባምንጭ)

– ኮከብ ግብጠባቂ – ሠራዊት ሳያ (አርባምንጭ)

– ኮከብ ተከላካይ –  አመንቲ አበት (ኦሮምያ)

– ኮከብ አማካይ – ሚኪያስ ኦፉይሳ (ደቡብ)

–  ኮከብ አጥቂ – ዮሴፍ ታረቀኝ (አዳማ ከተማ)

– የውድድሩ ምርጥ ቡድን – ደቡብ ክልል

– የውድድሩ ምርጥ ዕደሜ – ጋምቤላ 

– ኮከብ ዳኞች በሴት – ዮርዳኖስ ሙሉጌታ (ዋና ዳኛ) ገነት ቀሬ (ረዳት ዳኛ)

– ኮከብ ዳኞች በወንዶች – አብዱራህማን ይማም (ዋና ዳኛ)  – ተመስገን ኤዲኦ (ረዳት ዳኛ)

– ኮከብ የጨዋታ ታዛቢ –  ወልደሚካኤል መስቀሌ

– የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ አዳማ ከተማ


* የውድድሩ ልዩ ተሸላሚዎች

– የረጅም ዕድሜ የውድድር ፎቶግራፈር – አቶ ተሰማ

-የእግርኳስ ዳኞች ቅን አሳቢ እና ብዙ ዳኞች እንዲፈሩ ደከመኝ የማይለው የመብት ተከራካሪ – ሚካኤል አርዓያ