በኢትዮጵያ ቡና የዛሬው ጨዋታ ቡድን መሪው ማን ይሆናል ?


በቅርቡ ከቡድን መሪው ጋር የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ የቡድን መሪ ሚናውን ማን ይወጣለት ይሆን?

በካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ ዛሬ አስር ሰዓት ላይ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ ከዩጋንዳው ዩአርኤ ጋር የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ቡናማዎች አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የካፍ መስፈርትን አለሟሟላቱን ተከትሎ ከተመልካች ጋር ቁጭ ብሎ ጨዋታውን የመከታተል ግዴታ ውስጥ ገብቷል። በዚህም ምክንያት የግብጠባቂው አሰልጣኝ ፀጋዘአብ አስገዶም ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሁለት ሥራዎችን ደርቦ የሚሰራ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ ዜና ደግሞ ያለፉትን ሦስት ዓመት የኢትዮጵያ ቡናን ቡድን መሪ በመሆን ያገለገለው ዘሪሁን በቅርቡ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መልቀቂያ በማስገባቱ ከቡድኑ ጋር ወደ ዩጋንዳ አልተጓዘም። ይህን ተከትሎ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ ክለቡ በጊዜዊነት ምክትል አሰልጣኙ ገብረኪዳን ነጋሽን ቡድን መሪ እንዲሆን አድርጓል። ገብረኪዳን ነጋሽ እንደ ፀጋዘአብ ሁሉ በዛሬው ጨዋታ ሁለት ሥራዎች ደርቦ እንደሚሠራ ይጠበቃል።

ከሜዳ ውጭ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስቀድሞ ማለቅ አለመቻላቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከአስር ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ መድረክ የተመለሰበትን አጋጣሚ ለመከወን ባልተሟላ ሁኔታ ካምፓላ ይገኛል።