ኢትዮጵያ ቡና ለአማካይ ተጫዋቹ የደሞዝ እርከን ማሻሻያ አደረገ

ከመከላከያ በ2012 ኢትዮጵያ ቡናን በአነስተኛ የደሞዝ ለተቀላቀለው አማካይ የወርሀዊ ደሞዝ እርከኑ ላይ ማሻሻያ ተደርጎለታል።

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የእግርኳስ ህይወቱን መነሻ በማድረግ በመከላከያ ተስፋ ቡድን እና ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ዊልያም ሰለሞን በ2012 ኢትዮጵያ ቡናን ለሦስት ዓመት ለማገልገል ፊርማውን ማኖሩ ይታወቃል። በጊዜው ዊልያም ከቡናማዎቹ ጋር ሲፈራረም በአነስተኛ ወርሀዊ ደሞዝ የነበረ ሲሆን በሁለቱ አካላት አስቀድሞ በተደረገው ስምምነት መሠረት ዊልያም በየዓመቱ የሚሰጠው ወቅታዊ ብቃቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ እንደሚያደርግ ክለቡ ከተጫዋቹ ጋር ስምምነት መድረሱ ይታወቃል።

በዚህም መሠረት ዊልያም ሰለሞን ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ እያሳየው ባለው ጥሩ ግልግሎት መነሻነት መጠኑ በሁለቱ አካላት ባይገለፅም የቆይታ ዘመኑ ሳይነካ አሁን የሚከፈለው ወርሀዊ ደሞዝ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል በአንደኛ ደረጃ እርከን ላይ ተከፋይ ከሆኑ ተጫዋቾች እኩል እንዲያገኝ ተደርጓል። ዊልያም በካፍ ኮፌዴሬሽን ካፕ ከሜዳው ውጭ ከዩጋንዳው ዩአርኤ ጋር 2-1 በተረታበት ጨዋታ ላይ ለቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ተስፋን የሰነቀችውን ብቸኛ ጎል ማስቆጠሩ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ይህ የተለመደ አሰራር ሲሆን ከዚህ ቀደም ከታችኛው ቡድን ላደጉ እና እንዲሁም ከሌላ ክለብ ላመጣቸው ተስፈኛ ተጫዋቾች ደሞዝ ማሻሻሉ ይታወቃል።