በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ለበርካታ ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ግብ ጠባቂ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ጅማ አባጅፋርን መዳረሻው ለማድረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከሾሙ በኋላ አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው በመቀላቀል የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት ጅማ አባጅፋሮች ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ወደ ዝውውር ገበያው ከወጡ ሰነባብተዋል። ክለቡ በቦታው ተጫዋች ለማግኘት ያደረገው እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶም ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራን የግሉ ለማድረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የተጫዋቹ ወኪል ሳምሶን ነስሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።
ከ2003 አጋማሽ እስከ 2010 ድረስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ቆይታ ያደረገው ሮበርት ኦዶንካራ ለ5 ጊዜያት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከፈረሰኞቹ ጋር ማንሳቱ አይዘነጋም። ከዚህ ጎን ለጎን አምስት ጊዜያት የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ክብርን አግኝቶ እንደነበር ይታወቃል። ተጫዋቹ ሰባት ዓመት ከግማሽ ካገለገለበት ክለብ ከወጣ በኋላ ደግሞ በአንድ ዓመት ውል ወደ አዳማ ከተማ አቅንቶ መጫወቱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ሦስተኛ ክለቡ ወደሚሆነው ጅማ ለማቅናት ተስማምቷል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በ16 ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ባለሪከርዱ ኦዶንካራ ነገ ምሽት ኢትዮጵያ እንደሚገባ የታወቀ ሲሆን ከነገ በስትያም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ፊርማውን እንደሚያኖር ተጠቁሟል።