“ከዚህ ቀድም ከተደረገው ውድድር የተሻለ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል” – የአአ/እ/ፌ ፕሬዝዳንት አሥራት ኃይሌ

በስምንት ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን አስመልክቶ የምድብ ድልድል ይፋ የማድረግ እና ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የተሰጠበት መድረክ ዛሬ ከሰዓት ተካሂዷል።

በቤስት ዌስተርን ሆቴል በተካሄደው የምድብ ድልድል የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ ዣንጥረር ዓባይ፣ የስፖርት ኮሚሽን ከሚሽነር በላይ ደጀን፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አሥራት ኃይሌ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመውበታል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አሥራት ኃይሌ የዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በሁሉም መልኩ የተለየ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው “ውድድሩ ስኬታማ እንዲሆን የከተማዋ አስተዳደር የአአ ስፖርት ኮሚሽን እና ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ትልቁን ስራ ሲሰሩ ስለቆዩ ከወዲሁ ማመስገን እፈልጋለው።” በማለት አጭር ንግግር በማድረግ ለስፖር ኮሚሽን ከሚሽነሩ አቶ በላይ ደጀን መድረኩን ለቀዋል።

አቶ በላይ በበኩላቸው የዘንድሮው የከተማው አስራ አምስተኛ ዋንጫ ያማረ እንዲሆን ከወራት በፊት ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር ሲመክሩበት እንደነበረ አውስተው የከተማው ስፖርት ኮሚሽን ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት በልዩ ሁኔታ የሚከታተለው እንደሆነ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። የዘንድሮን ውድድር ለየት ለማድረግ ብዙ ነገሮች እንደተሰሩ እና ወንድማማችነት መንፈስ እንዲኖረው ለማድረግ ከሀገር አልፎ የጎረቤት ሀገራት ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ጥሩ ጅምር እንደሆነ ገልፀዋል።

በማስከተል የዕለቱ የክብር እንግዳ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ ዣንጥራ ዓባይ በንግግራቸው የከተማው አስተዳደር ለዚህ ውድድር ልዩ ትኩረት መስጠቱን እና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከተማዊ በመሆኑ የከተማችንን ገፅታ በሚገነባ መልኩ የስፖርታዊ ጨዋነትንና አርአያነትን ይዞ በስኬት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፎች ሁሉ ያደርጋል ብለዋል። የ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ሲቲ ካፕ ውድድር ልዩ ትዝታን ወንድማማችነትንና ሰላምን ይዞ እንዲካሄድ ከጅምሩ የላቀ ሚና እየተጫወቱ ለሚገኙት ለአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እግርኳስና ወጣቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው በዘንድሮው 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሚወክለው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከተማችንን ወክሎ በተቀላቀለ ወቅት ሲቲ ካፑ መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገውም አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል ።

ከክብር እንግዶቹ የመክፈቻ ንግርግር በኃላ የተለየዩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የቀረበ ሲሆን በመድረኩም የነበሩት አካላት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ደማቅ ውድድር ምን የተለየ ነገር እንጠብቅ ?

” ከዚህ ቀድም ከተደረገው ውድድር በተሻለ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። በየጨዋታ የኮከብ ምርጫ በተለየ ዲዛይን የተሰሩ ዋንጫዎች ተዘጋጅተዋል። ሌሎች የሚካተቱ ነገሮችንም ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን። እንደጨረስን እናሳውቃለን። በውድድሩ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ ተመልካች በከፊል እንደሚገባ ታቅዷል። ብዛቱ ከጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር የሚወሰን ይሆናል። የመክፈቻው መርሐግብር ደማቅ እና ሳቢ በሆነ መንገድ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።”

የተሳታፊ ክለቦች ማረጋገጫ

” ስምንቱም ክለቦች በዚህ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ ሰጥተውናል። ባህር ዳር ከተማና ኢትዮጵያ ቡና በሲዳማ ካፕ እንደሚሳተፉ ተሰምቶ ነበር። ሆኖም ግን መቶ ፐርሰንት በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ። ማረጋገጫ አግኝተናል። ”

ቀጥታ ስርጭት

” ውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዲያገኝ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው። በቅርቡ የደረስንበትን እናሳውቃለን። ያም ቢሆን ውድድሩ የቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ይሆናል።”

 የስታዲየም መግቢያ 

“ትኬቶች በአሞሌ በኩል ሽያጩ የሚፈፀም ሲሆን የመግቢያ ዋጋውም ክቡር ትሪቡን 500፣ ሁለቱም ጥላ ፎቅ 300፣ ከማን አንሼ 200፣ ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎች በ100 ብር ይሆናል። የሙሉ ጨዋታ ትኬት ለሚገዙ አንድ ጨዋታ ነፃ ይደረጋል።”

በመቀጠል የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱን የእግርኳሱ አንባሳደሮች እንደ የቅድመ ተከተላቸው በማውጣት መርሐ ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።

በወጣው ድልድል መሠረት :-

ምድብ ሀ

ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ ፣ ሙኑኪ ኤፍ ሲ (ደቡብ ሱዳን)

ምድብ ለ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ