ስልጤ ወራቤ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ የሚገኘው ስልጤ ወራቤ አዲስ አሰልጣኝ በይፋ ቀጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሐ ከተደለደሉ አስራ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ስልጤ ወራቤ ያለፉትን ሦስት አመታት በወጣቱ አሰልጣኝ አብዱልወኪል አብዱልወሀብ እየተመራ መዝለቁ ይታወሳል፡፡የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በምድቡ በ24 ነጥቦች 9ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ክለቡ በቀጣዩ የ2014 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ካለፉት ዓመታት የተሻለ ሆኖ ለማጠናቀቅ እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት እቅድ የያዘ ሲሆን ለዚህም ይረዳው ዘንድ የአሰልጣኝ ቅጥርን መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ በሊጉ ውጤታማ ታሪክ ያላቸው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ (መንቾ) ደግሞ የክለቡ አዲሱ አለቃ ሆነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሀድያ ሆሳዕናን በሁለት አጋጣሚ እንዲሁም ደግሞ ደቡብ ፖሊስን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በማሳደግ የሚታወቁት አሰልጣኝ ግርማ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ የምድብ ለ ተካፋይ በሆነው ሀምበሪቾ ዱራሜ ቆይታ በማድረግ እና ቡድኑን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ያደረጉ ሲሆን ለቀጣዩ የ2014 የውድድር ዘመን ደግሞ የስልጤ ወራቤ አሰልጣኝ በመሆን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅለዋል፡፡