ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ልምምዳቸውን ሰርተዋል

ነገ 10 ሰዓት የዓለም ዋንጫ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት የምድብ ሦስተኛ ጨዋታውን ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል። ከመስከረም 15 ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚያደርገው ተከታታይ ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ረፋድ ላይ ሰርቷል።

ከ3:30 ጀምሮ በተከናወነው ልምምድ ላይ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾቹ ከኳስ ጋር እንዲያፍታቱ ካደረጉ በኋላ በሦስት ቦታ ቡድኑን በመክፈል አዝናኝ መሐል ባልገባ ጨዋታ እንዲከውኑ አድርገዋል። በመቀጠል ደግሞ የፍፁም ቅጣት ምት አካባቢ የሚገኙ ኳሶችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል እንዲሁም ከቅጣት ምት እና ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረጉ ኳሶች ለማስቆጠር የሚያስችል የልምምድ መርሐ-ግብር ሲያሰሩ ነበር። ቀለል ያለ እንቅስቃሴ የተደረገበት የቡድኑ የጠዋት ልምምድም 5 ሰዓት ሲል ፍፃሜውን አግኝቷል። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ በታዘበችው መሠረት ቡድኑ ውስጥ ምንም አይነት የጉዳት ዜና የለም።

ጠዋት 2 ሰዓት ባህር ዳር ዐየር ማረፊያ የደረሰው የደቡብ አፍሪካ ልዑክ ደግሞ ማረፊያውን በኩሪፍቱ ሪዞርት ካደረገ በኋላ ከአመሻሽ 10 ሰዓት ጀምሮ ልምምዱን በባህር ዳር ስታዲየም ሰርቷል።