የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ

ቀጣዩ የውድድር ዓመት የዳሰሳችን ትኩረት ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰው መከላከያ ሆኗል።

ከ1997 ጀምሮ ለ15 ዓመታት ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ በሊጉ የዘለቀው መከላከያ 2011 ላይ ነበር ወደ ከፍተኛ ሊጉ የወረደው። በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ የረጅም ዓመታት ባለታሪክ የሆነውና ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ አደረጃጀት በ1990 ከመጀመሩ በፊት 11 የጊዜ ቻምፒዮን መሆን የቻለው ክለቡ የ2012 የውድድር ዓመት በኮቪድ ወረርሺኝ ምክንያት በመቋረጡ በከፍተኛ ሊጉ ሙሉ ተሳትፎ ያደረገው ዐምና ብቻ ነበር። በ2013ቱ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ምድብ ሀ ላይ ተደልድሎ የነበረ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ኢትዮ ኤሌክትሪክን በቅርብ ርቀት ሲከተል ቆይቶ ሁለተኛው ዙር ላይ ማርሽ ቀይሮ መጥቷል። ተከታታይ ድሎችን እያመዘገበ ዙሩን ያለሽንፈት በማገባደድ የነጥብ ስብስቡን 38 አድርሶ በመጨረሱም በቤትኪንግ ስም በተሰየመው ቀዳሚው ሊግ የሚያሳትፈውን ትኬት ለመቁረጥ በቅቷል።

መከላከያ ወደ ሁለተኛው የሊግ እርከን ሲወርድ ወደ ኃላፊነት የመጡት እና ውጥናቸው ሰምሮ ወደ ነበረበት የመለሱት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ዘንድሮም አብረውት ይዘልቃሉ። ምክትል አሰልጣኙ ዮርዳኖስ ዓባይም እንደ ዋና አሰልጣኙ ሁሉ ከጦሩ ጋር ሲቀጥሉ አሰልጣኝ አምሳሉ እስመለዓለምም በተጨማሪ ምክትል አሰልጣኝነት ተቀላቅለዋል። የቀድሞው ግብ ጠባቂ በለጠ ወዳጆ በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝነት ፣ ዶ/ር ጌታዬ ተመስገን እና ሻምበል ደጀኔ አበበ በህክምና ባለሙያነት እንዲሁም ሻለቃ ዓለሙ ዘነበ በቡድን መሪነት የምንመለከታቸው የቡድኑ አባላት ናቸው።


መከላከያ ከከፍተኛ ሊጉ ሲያድግ ከበርካታ ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል። ከእነዚህም ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበራቸው እንደ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ በኃይሉ ግርማ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ ሰለሞን ሀብቴ፣ መሐመድ አበራ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬ ዓይነቶቹ ወደ ተለያዩ ክለቦች ሲያመሩ እነካርሎስ ዳምጠው እና ኑሁ ፉሰይንን ጨምሩ አራቱም የውጪ ዜጎች በዘንድሮው መከላከያ ውስጥ አናገኛቸውም። ይህ በመሆኑም አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በፕሪምየር ሊጉ ይዘው የሚቀርቡትን ቡድን ለማሟላት በርከት ያሉ ግዢዎችን እንዲፈፅሙ መነሻ ሆኗል። በዚህም ጋናዊው ክሌመንት ቦዬ እና ሙሴ ገብረኪዳን የቡድኑ አዲስ ግብ ጠባቂዎች ሲሆኑ ዳዊት ወርቁ፣ ቢኒያም ላንቃኖ እና ልደቱ ጌታቸው የተከላካይ ክፍሉን ለማጠናከር ጦሩን ተቀላቅለዋል። የክለቡ ዝውውር ይበልጥ ትኩረት በሰጣቸው ቀሪዎቹ ክፍሎቹ ላይ ደግሞ ኢማኑኤል ላሪያ፣ ዓለምአንተ ካሣ፣ ደሳለኝ ደበሽ እና ቢኒያም በላይ በአማካይነት ሲፈርሙ አጥቂ ክፍሉ ኢማኑኤል ኦኩቱ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ፣ አዲሱ አቱላ፣ ገዛኸኝ ባልጉዳ፣ ብሩክ ሰሙ እና አኩዌር ቻምን ያካተተ ሆኗል።

ከአዲሶቹ ውስጥ ከዚህ ቀደም አብረዋቸው የሰሩ ተጫዋቾች በቁጥር ከአምስት እንደማይበልጡ የሚያነሱት አሰልጣኝ ዮሐንስ የተደረጉትን ዝውውሮች ከልምድ አንፃር ሲመዝኗቸው “ዝውውሮቻችን የተደባለቁ ናቸው። በብዛት ወጣቶች አሉን። የተወሰኑ ደግሞ ልምድ ያላቸው አሉን። በተለይ ብዙ ጊዜ የሚያገለግሉንን ወጣቶች እና ጥሩ ሥነ-ምግባር እና ልምድ ያላቸውንም ይዘናል። በአጠቃላይ ምጥጥኑ 1ለ3 ነበር ማለት ይቻላል። 1 ልምድ ያለው 3 ወጣቶችን ነው ያመጣነው።” ይላሉ።

አሰልጣኙ ከአምናው ቡድናቸው ውስጥ አብረዋቸው የቀጠሉ ባይጠፉም የአዲሶቹም ቁጥር ቀላል የሚባል ባለመሆኑ አዲስ ስብስብን ወደ ተፎካካሪ ቡድንነት የመቀየር ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል። ከስብስብ ጥራት አኳያ የ2014ቱን መከላከያ ወረቀት ላይ ስንመለከተው ደግሞ ከዚህ ቀደም በሊጉ ከነበሩት ቡድኖቹ ጋር ሲተያይ የቀነሰ ይመሳል። በነበሩባቸው ክለቦች ራሳቸውን በሚገባ ያላስመሰከሩ ተጫዋቾች መበራከታቸውም አንዱ ማሳያ ነው። እርሳቸው ግን ከተጫዋቾቹ ነባር እና አዲስነት ወይንም የቀደመ አቋማቸው ይልቅ የሥራ ባህል ቡድኑንን ለማዋቀር ቁልፉ ነጥብ እንደሆነ አጥብቀው ያምናሉ። “ካለኝ ልምድ አንፃር አንድ ቡድን ላይ ነባርም ሆነ አዲስ ተጫዋች ያዝክ እግርኳሳችን ሥራ ይፈልጋል። ማንንም ብትይዝ ትልቁ ነጥብ ላብህን ጠብ አድርገህ መስራት አለብህ ፤ የላብህን ዋጋ ነው የምታገኘው። በዚህ ላይ ሊረዱህ የሚችሉ ልምድ እና ስርዓት ያላቸው ተጫዋቾች ያስፈልጉሃል ፤ ያንተን ሀሳብ እንዲያሳኩልህ። ከዛ ውጪ ወጣቶቹ ፍላጎታቸው ጠንካራ ነው።”

አሰልጣኝ ዮሐንስ ወጣቶችን በስብስባቸው ውስጥ ከመያዝ ባለፈ በድፍረት ዕድል ለመስጠት ኃላፊነት ሲወስዱ ይታያል። ለአብነት ያህል በአሁኑ ቡድናቸው ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም በወልዋሎ ሳሉ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመጣው ብሩክ ሰሙ እና እዛው በነበረው ሠመረ ሀፍተይ ላይ ያሳዩትን ዕምነት ማንሳት ይቻላል። በመሆኑም በዘንድሮው መከላከያ ውስጥ በተከላካይነት ትንሣኤ አዲሱ፣ አብርሀም ከላይነህ በአማካይነት ዮሐንስ መንግሥቱ በአጥቂነት ኢብራሂም መሐመድ እና እንዳልካቸው ጥበቡ የተካተቱት ወጣቶች ዓመቱ የእግርኳስ ህይወታቸው የሚፈነጥቅበት ሊሆንላቸው ይችላል። አሰልጣኙም “አሁን 5 ታዳጊዎችን በስብስባችን ይዘናል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይም ሞክረናል። ያሉትም በብዛት አዲስ ሆነው ወጣቶች ናቸው። ጀማሪዎቻችንም እንኳን በሌሎች ክለቦች ብዙ የመጫወት ዕድል ያላገኙ ናቸው። በእነሱ ላይ ደግሞ ሌላ ወጣቶች እንዳልኩህ አሳድገናል። ስለዚህ ፉክክሩ ጥሩ ይሆናል ብዬ ነው የምገምተው። ቡድኑ ውስጥ ያለው ፍላጎትም ከፍተኛ ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም በማስተማር ደረጃ ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ ነው።” በማለት በወጣት ስብስባቸው ላይ ያላቸውን ተስፋ ያመለክታሉ።

መከላከያ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከወርኃ ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ መቀመጫውን በቢሾፍቱ በማድረግ እየከወነ ይገኛል። የቡድኑ ዋነኛ ትኩረትም የነበረው አዲሶቹን ከነባሮቹ የማናበብ የውህደት ሥራ ነበር። ከዚህ ጎን ለጎንም አስራሦስት ለሚሆኑ ወጣቶች ዕድል በመስጠት ሲመዝን ቆይቷል። በመጨረሻም ራሱን በውድድር ለመፈተን የአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው መከላከያ እስከፍፃሜው በመዝለቅ ራሱን በአምስት ጨዋታዎች ከሊጉ ሌሎች ክለቦች አንፃር የመፈተሽ ዕድልን አግኝቶ ውድድሩን በሁለተኝነት አገባዷል።


ከጨዋታ መንገድ ምርጫ ጋር በተያያዘ መከላከያን ከአንድ አጨዋወት ጋር ማያያዝ ይከብዳል። አሰልጣኙም ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው ቡድን በመገንባት ስላላቸው እምነት በሰፊው አብራርተዋል። “እኛ ቡድን ውስጥ ስንዘጋጅ ለውድድር ነው የምንዘጋጀው። ይሄ ዓይነት ብለን አንድ አጨዋወት አናስቀምጥም። ምክንያቱም የምንገጥመው ቡድን በሙሉ አንድ ዓይነት አጨዋወት ስለሌለው። ሌላው ቀርቶ አንድ ቡድን ራሱ እኛ እንዳለን ሁለት ሦስት ዓይነት የአጨዋወት ዘዴ አለው። እኛም በተመሳሳይ ሁለት ሦስት ዓይነት የአጨዋወት ዘዴ ነው ያለን። ስለዚህ በጊዜ የምንገጥማቸውን ቡድኖች ብዙ ስለማናውቃቸው በተለያየ መንገድ ራሳችንን እናዘጋጃለን። ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቡና አንድ ዓይነት አጨዋወት አይከተሉም። ስለዚህ በእኛ ግምት ለሁለቱም አንድ ዓይነት አጨዋወት ይዘህ አትገባም። እያንዳንዱ አሠልጣኝ የየራሱ አጨዋወት አለው። እዚህም ጋር ነው አሠልጣኝ አዕምሮውን የሚጠቀመው። እኛ የምንዘጋጀው ባላጋራችን ምን ይዞብን ይመጣል ብለን ነው። ያንን ደግሞ አሸንፈን እንድንወጣ እኛ ምን ይዘን መግባት አለብን በሚለው እናስባለን። እንጂ አንድ ዓይነት ብቻ አጨዋወት የለንም።”

ይህን ተለዋዋጭ ባህሪ እንደ አስፈላጊነቱ ለመተግበር የስብስቡ ስብጥር ለሁሉም የጨዋታ ምርጫዎች እንዲመች የሚያደርግ ምልመላ ያስፈልገዋል። ከዚህ አንፃር መከላከያ ከሌሎች ክለቦች ጋር ሲተያይ የላቀ የሚባል በአማራጬች የተሞላ ቡድን አለው ለማለት አያስደፍርም። ነገር ግን አሰልጣኙ ተጫዋቾች ከአንድ በላይ ኃላፊነት የመወጣት ብቃት እንዲኖራቸው የማድረግ ዕምነት ተከታይ መሆናቸው ያሰቡትን ተለዋዋጭነት ለመተግበር ጥሩ ግብዓት እንደሚሆንላቸው ይገመታል። “በረኛችን አጥቂ ሆኖ ብታየው እንዳይገርምህ። ኳስ ጨዋታ እስከሆነ ጊዜ አንድ ተጫዋች አስራ አንድ ቦታ ሳይሆን ሦስት ቦታዎች ነው ያሉት ከበረኝነት ውጪ። ተከላካይ አማካኝ ወይም አጥቂ። ከሦስቱ ከአንድ ሁለት መጫወት የሚችል ነው። አሁንም ይሄንን ልምምድ ላይ እያደረግነው ነው። ተከላካይ ሆኖ መሐል እንዲጫወት አማካይም ሆኖ ፊት እንዲጫወት እያደረግን ነው። አንደኛ እግርኳስ እንዳይሰለች ያደርጋል። ሁለተኛ ልጆቹንም ቻሌንጅ ስታደርጋቸው የተሻለ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ። በአንድ ቦታ ብቻ የሚጫወት ተጫዋች ሁል ጊዜ አዕምሮው ይገደባል። እንዳይገደብ እና አዳዲስ ነገሮችን የመማር ፍላጎቱ እንዲመጣ ይህንን እናደርጋለን። ተጫዋች እኮ አንድ ቦታ የሚጫወተው አሠልጣኝ ስለሚለው ነው እንጂ ተጫዋች ሲፈጠር እዚህ ቦታ ነው ተብሎ አይደለም። አንድ ቡድን ውስጥ አጥቂ ሲታጣ ተከላካዩ አጥቂ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ተጫዋቾቹን ቻሌንጅ ለማድረግ እና ጥሩ እንዲሰሩ በማሰብ ነው። ሲጀምር ተጫዋቾቹም እዚህ ቦታ ብታጫውተኝ የሚሉም አሉ። አንዳንዴ ደግሞ በአንድ ቦታ ሁለት ጎበዝ ተጫዋቾች ይኖራሉ። አንዱ ተሰልፎ አንዱ ከሚቀመጥ ሁለቱንም ለማሰለፍ ለአንደኛው ለምን ሌላ ቦታ አንፈልግም በሚል ሀሳብ ነው የምንሰራው። ይህ በዚህ ዓመትም ሊታይ ይችላል።” የሚለው ዘርዝር ያለ ማብራሪያቸውም የቡድኑ ተለዋዋጭነት በምን ላይ እንደሚመሰረት በቂ ጥቆማ ይሰጣል።


በመከላከያ የዘንድሮው ቡድን ውስጥ ጎልተው ሊወጡ የሚችሉ ተጫዋቼችን ስናነሳ በአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች እንደሚሆን ፍንጭ ያሳየው ቢንያም በላይን እናገኛለን። በበርካታ የማጥቃት አማራጮች ላይ መሰለፍ የሚችለው ቢንያም ቡድኑ በሚኖረው ተለዋዋጭነት ውስጥ የጎል ምንጭ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቅል። ሠመረ ሀፍተይ ሌላው ዓይን ውስጥ የሚገባ ተጫዋች ነው። ወጣቱ የመስመር ተጫዋች በአሰልጣኝ ዮሐንስ ስር በወልዋሎ ድንቅ ጅማሮ ማድረጉ ሲታወስ አሁንም በአሰልጣኙ ክትትል ስር መሆኑ ዕድገቱ ከፍ ብሎ እንደሚመጣ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በሲዳማ ቡና ቤት ክህሎቱን ያሳየው ሆኖም ዕድገቱ በከፍታ ሲዘልቅ ያልተመለከትነው አዲሱ አቱላም ራሱን በአግባቡ የሚያሳይበት ዓመት ከፊቱ ይጠብቀዋል። የምክትል አሰልጣኙ ዮርዳኖስ አባይ መኖር ደግሞ ለአጥቂዎቹ ትልቅ እገዛ እንዳለው ዕሙን ነው።

ከውጤት አንፃር ከታች እንደመጣ ቡድን በሊጉ የመቆየት ዓላማን ይዞ ወደ ውድድር መግባት ለመከላከያ የማይታሰብ መሆኑን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አበክረው ይናገራሉ። በፉክክሩ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ የሆነ ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡም ሲናገሩ ” የምንጫወተው ጥሩ ውጤት አምጥተን ተፎካካሪ ለመሆን ነው። ከወገብ በላይ ምናምን የሚባለው ከዚህ በፊት የነበሩ ሰዎች ያደረጉት ነው። እኛ ግን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ለመቅረብ ነው። ሁሉም ከ0 ነው የሚጀምረው። ማንም ነጥብ ይዞ የሚመጣ የለም። ሁሉም ክለብ ዕኩል ጨዋታ ነው የሚያደርገው። ስለዚህ ለ30ው ጨዋታ ማግኘት የሚገባንን ለማግኘት ነው የምንጫወተው እንጂ ካሁኑ ለዚህ ደረጃ አንልም። ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ አቅማችን በፈቀደውን ሁሉ እንሰራለን። ሊጉ ለሁሉም ክፍት ነው። ቻምፒዮን ለመሆንም ሆነ ለመውረድ። ይህ እስከሆነ ድረስ ከላይ ወደ ታች ሥራችንን እንሰራለን። አቅማችን በፈቀደው ሁላ ማድረግ የሚገባንን በማድረግ እንጫወታለን። እንዳልኩት ዘንድሮ ተፎካካሪ ለመሆን ነው የምናስበው። አዲስ የመጣን ነን እና ላለመውረድ እንጫወታለን አንልም። ሁሉም ዕኩል ዕድል ነው ያለው። የሰራው እና የተሻለው ያሸንፋል የሚል ዕምነት አለኝ።” ይላሉ።

በዚህ መልኩ የዓመቱን ግቡን አስቀምጦ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብቅ የሚለው መከላከያ በመጪው ሰኞ ጨዋታዎቹን ማድረግ ሲጀምር ከሌላኛው አዳጊ አርባምንጭ ከተማ ጋር ይገናኛል።

የመከላከያ የ2014 ስብስብ

 

ግብ ጠባቂዎች

1 ጃፋር ደሊል
29 ሙሴ ገብረኪዳን
30 ክሌመንት ቦዬ

ተከላካዮች

2 ኢብራሂም ሁሴን
4 አሌክስ ተሰማ
11 ዳዊት ማሞ
12 ቢንያም ላንቃሞ
13 ገናናው ረጋሳ
19 ልደቱ ጌታቸው
16 ዳዊት ወርቁ
23 ትንሣኤ አዲሱ (U-23)
27 አብርሃም ከላይነህ (U-23)

አማካዮች

5 ግሩም ሐጎስ
6 ዓለምአንተ ካሣ
20 ዮሐንስ መንግሥቱ (U-23)
22 ደሳለኝ ደበሽ
24 ቢንያም በላይ
25 ኢማኑኤል ላርዬ
28 ኪም ላም

አጥቂዎች

7 ብሩክ ሠሙ
9 ገዛኸኝ በልጉዳ
10 አዲሱ አቱላ
14 ሠመረ ሀፍታይ
15 ኢብራሂም መሐመድ (U-23)
18 ኦኩቱ ኢማኑኤል
21 አቤል ነጋሽ
26 አክዌር ቻም
38 እንዳልካቸው ጥበቡ (U-23)
99 ኤርሚያስ ኃይሉ