የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበት ቀን ታውቋል

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሁለቱም ዲቪዚዮኖች የሚጀመርበት ቀን ይፋ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በርካታ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለመጀመር አቅደው ፕሪምየር ሊጉ የሚጀመርበትን ቀን አለማወቃቸው እክል እንደፈጠረባቸው በተደጋጋሚ ሲገልፁ የነበረ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ ከነባሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ልማት እና ውድድር ኮሚቴ ጋር በትላናንትናው ዕለት ባደረገው ስብሰባ ክለቦች በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ለነበረው ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት አስራ ሶስት ክለቦችን ተሳታፊ የሚደርገው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን እና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተወዳድረው ያደጉን ስድስት ክለቦች አካቶ በድምሩ አስራ ስድስት ክለቦችን የሚያካፍለው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድሮች በተመሳሳይ ታኅሳስ 17 እንዲጀመር ፌዴሬሽኑ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ ገልጿል፡፡

ምንም እንኳን የሚጀመርበትን ቀን ይፋ ቢደረግም ክለቦች አስቀድመው ማድረግ ያለባቸውን ምዝገባ ከጥቂት ክለቦች ውጪ ተግባራዊ እያደረጉ ባለመሆኑ በቀሩት የምዝገባ ቀናት መመዝገብ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡