የሉሲዎቹን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ለሚጠብቀው የ2022 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲሆን ይህን አስመልክቶም ዛሬ በአሰልጣኙ እና አምበሏ አማካኝነት መግለጫ ተሰጥቷል። 

ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር በመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ የማጣርያ ጨዋታ የሚጠብቃቸው ሉሲዎቹ መቀመጫቸውን በካፍ የልህቀት ማዕከል በማድረግ ዝግጅት ማድረግ ከጀመሩ የሰነባበቱ ሲሆን ከአምስት ቀን በኋላ ለሚጀምሩት የማጣርያ ጉዞ የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው መሪነት እየተዘጋጁ የሚገኙት ሉሲዎቹ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾቻቸውን የለዩ ሲሆን ስለ አጠቃኣይ ዝግጅታቸው ዛሬ በፌዴሬሽኑ ከአምበሏ ሎዛ አበራ ጋር ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የተጫዋቾችን ምርጫ በተመለከተ ሀሳብ በማንሳት ማብራርያቸውን የጀመሩት አሰልጣኝ ብርሃኑ ምርጫው የተከናወነው የ2013 ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ማዕከል ባደረገ መልኩ መሆኑን ገልፀው ውድድሩ ካለቀ በኋላ ተጫዋቾችን ተመልክቶ ምርጫ ለማከናወን የሚያበቃ ውድድር ባለመኖሩ የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና የንግድ ባንክ የሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮእስ ሊግ ማጣርያ ላይ ለመመርኮዝ መሞከራቸውን ገልፀዋል። ”በቅድሚያ 34 ተጫዋቾች ነበር የጠራነው። ስድስቱ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ነበሩ። እነሱ እስኪመጡ ድረስ በ27 ተጫዋቾች ስንዘጋጅ ቆይተናል። አንዷ (ዓባይነሽ ኤርቄሎ) ደግሞ ምክንያቷን ሳትገልፅ ሳትመጣ ቀርታለች። በትናንትናው ዕለት 23 ተጫዋቾችን ለይተን ለፌዴሬሽን ስም አስገብተናል። ከስብስባችንም ውስጥ አምስት ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዘናል። ሌሎቹ 18 ተጫዋቾች ደግሞ ወጣት እና ታዳጊዎች ናቸው። አብዛኛዎቹ የብሔራዊ ቡድን ልምድ ያላቸው ቢሆንም በእድሜ ወጣት መሆናቸው ለውጤታማነታችን ወሳኝ ናቸው ብዬ አስባለሁ።፤ ሲሉም አክለዋል።

ፕሪምየር ሊጉ ካለቀ በኋላ ለረጅም ጊዜ ከውድድር መራቃቸውን እንደ ችግር ያነሱት አሰልጣን ብርሃኑ ክረምት ላይ ተጫዋቾች ብዙም ራሳቸው ላይ ሰርተው ስለማይመጡ ሰውነታቸው ጨምሮ እንደሚመጡ የሚታወቅ ቢሆንም የያዟቸው ተጫዋቾች ራሳቸውን አዘጋጅተው በመምጣታቸው በዚህ ረገድ ችግር እንዳልገጠማቸው ተናግረዋል። የወዳጅነት ጨዋታ አለማግኘታቸው በዝግጅታቸው ወቅት እንደ ችግር ያነሱት ነጥብ ሲሆን ” ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ ሃገራት ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም። የኮሳፋ ውድድር ላይ ለመሳተፍ እድሉ ቢኖረንም ዩጋንዳ ልትሳተፍ ችላለች። ይህ አሁን ያለንበትን ደረጃ እንዳንመለከት አደርጎናል። ከሳይንስ አንፃር ባይደገፍም አማራጭ ስላልነበር ከወንዶች ታዳጊ ቡድን ጋር ተጫውተናል። ከጨዋታዎቹ ያገኘነው ውጤት ሳይሆን መታየት ያለበት በተጫዋቾቼ ላይ የውድድር መንፈስ እንዲኖር በማሰብ ነው ያደረግነው።” ብለዋል።

ከችግሮቹ ባሻገር የንግድ ባንክ ውድድር ላይ መቆየት እንደ መልካም አጋጣሚ የወሰዱት አሰልጣኙ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች እና ራሳቸውን ጨምሮ የንግድ ባንክ አባል መሆናቸው እና ጥሩ ውጤት አምጥተን መመለሳቸው መልካም ጎን እንዳለው አውስተዋል። ”በምስራቅ አፍሪካ አራት ንግስቶች አሉ። ሌሎቹ ገና ጀማሪ ናቸው። ኢትዮጵያ፤ ታንዛንያ፤ ኬንያ እና ዩጋንዳ የዞኑ ትልቅ ሃገራት ናቸው። በሴካፋው የገጠምናቸው ከሞላ ጎደል በብሐየራዊ ቡድን የምናገኛቸውን ነው። ከእነሱ ጋር ቻሌንጅ አድርገን ተጋጣሚዎቻችን ምን እንደሚመስሉ ያየንበት ነው። እንደ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነቴም ተመልሰን ምን አይነት ስራ መስራት እንዳለብን የተረዳሁት ነው።”

ከአሰልጣኙ ማብራርያ በኋላ አምበሏ ሎዛ አበራ ስለ አጠቃላይ ዝግጅታቸው በሰጠችው ሀሳብ ” ውድድር ካለቀ በኋላ ያለ ጨዋታ ረጅም የእረፍት ጊዜ አሳልፈናል። እንደ መልካም አጋጣሚ የነበረው የንግድ ባንክ የሴካፋ ውድደር ነው። ውጤቱም ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል። ይህንን መንፈስ እዚህ በማምጣት ከ20 ዓመት በታች ያሉትም ተቀላቅለው ጥሩ ስንሰራ ቆይተናል። ያለው መንፈስ ጥሩ ነው። ያለው ስብስብ የራሱን ታሪክ መፃፍ የሚፈልግ ስለሆነ ያንን ለማሳካት እየሞከርን ነው። አሰልጣኞቻችንም የሚያስፈልገንን እየሰጡ እኛም በአግባቡ እየተቀበልን እንገኛለን። እርስ በእርሳችን መከባበር እና ጥሩ የፉክክር መንፈስ አለ። ፉክክር ሲኖር ደግሞ የተሻለ ነገር መሥራት ይቻላል።” ብላለች።

ከአሰልጣኝ ብርሃኑ እና አምበሏ ሎዛ ማብራርያ በመቀቀጠል ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች መልሶችን ሰጥተዋል።

ስለ መከላከል ችግር

ብሔራዊ ቡድኑ የተወሰነ የትውልድ ክፍተት ነበረበት። ያንን ለመጠጋገን ሞክረናል። በአጥቂ ስፍራ ላይ የነበረውን ጥንካሬ እሁንም ቀጥሏል። አማካይ ላይ ደግሞ ወጣ ገባ የማለት ነገር ይታያል። በተለይ የፈጠራ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች በብዛት ያለማግኘት ነገር አለ። የመከላከል ላይ ደግሞ ችግር አለ። ሁላችንም እዚህ ላይ መስራት ይጠበቅብናል። አጥቂዎቻችን እንደሚያስፈሩ ሁሉ የኋላው ክፍልም ጠንካራ መሆን አለበት። ይህ ችግር የብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የእግርኳሱ ስለሆን የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች በጋር መስራት ይጠበቅብናል።

ክብደት የመጨመር

በቀን ሁለት ጊዜ ስንሰራ ቆይተናል። በአንድ ጊዜ የሚቀረፍ ባለመሆኑ ጊዜ ይፈልጋል። አማካይ ላይ የተጫዋች እጥረት ያለ በመሆኑ ያሉትን ከተውን ቦታው ክፍት በመሆኑ ለጊዜው ባለው ጠጋግነን ለመጓዝ ነው ያሰብነው።

ስለ ዩጋንዳ

በሴቶች እግርኳስ ላይ የተደራጁ ናቸው። በውጪ የሚጫወቱ እና በቅርቡ የተቀላቀሉ ተጫዋቾች አሏቸው። በቅርቡም የኮሳፋ ውድድር ላይም ተሳትፈዋል። እንቅስቃሴያቸውን በቪድዮ ስንከታተል ቆይተናል፤ የምስራቅ አፍሪካን የሴቶች እግርኳስ ሊቆጣጠር የሚችል ቡድን ነው። ስለዚህ ራሳቸውን በውድድር እያሳዩ የመጡ በመሆናቸው የምንገጥመው ጠንካራ ቡድን ነው። እነሱን ለማሸነፍ አዕምሯዊም መንፈሳዊም ጥንካሬ ያስፈልገናል። ያለን የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክ እኛ የተሻልን እንደሆንን የሚያሳይ ነው። እስካሁን አላሸነፉንም፤ አሁንም አያሸንፉንም።

ስለተጫዋቾቻቸው

ሁሉንም ተጫዋቾች ስንመለከት በጥሩ እድሜ ላይ ያሉ እና በዕድሜ እርከን ቡድኖች የተቃኙ ናቸው። ፍላጎትን በተመለከተ ከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ ናቸው። አፍሪካ ዋንጫ ላይ በመቅረብ የቀደሙትን ታሪክ ማሳካት ይፈልጋሉ። ሎዛን ለምሳሌ ብናነሳ ከሀገሯ አልፋ የዓለም መቶ ተዕዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ውስጥ መካተት የቻለች ተጫዋች ናት። ሆኖም አፍሪካ ዋንጫ ላይ እስካሁን አልታየችም። እነ ሜሲ እና ሮናልዶ በክለብ ደረጃ ያሳኩትን በብሔራዊ ቡድን አልደገሙም በሚል ሲተቹ እንደነበረው ሁሉ እነ ሎዛም በተመሳሳይ በወጣት ቡድን ካልሆነ በአፍሪካ ዋንጫ ደረጃ አላየናቸውም። አሁን ባለው ስብስብ የአብዛኛዎቹ በጥሩ ብቃት ላይ መድረስ ከነችግራችንም ቢሆን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወርቃማ ጊዜ ላይ ነን።

ስለ ወዳጅነት ጨዋታዎች

ባለፈው በሶከር ኢትዮጵያ ላይ ውበቱ አባተ በወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት አንድ ዓመት መድፈኑን እና ያደረገው ጨዋታ ብዛት በቁጥር ተደግፎ ስመለከት መንፈሳዊ ቅናት አድሮብኛል። እኔ ወደ ብሔራዊ ቡድን ከመጣሁ በኋላ እስካሁን በነጥብ ጨዋታ ደረጃ አሁን (ከዩጋንዳ ጋር የምናደርገው) ገና የመጀመርያ ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ 180 ደቂቃ ጨዋታ ብቻ ማከናወን አስቸጋሪ ነው። በፌዴሬሽኑም በኩል ጥረት ተደርጎ የወዳጅነት ጨዋታ ከዚህ ቀደም ተገኝቶ ቢሆንም ንግድ ባንክ ውድድር ላይ የነበረ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል።

ስላልመጣችው ተጫዋች

ከተጠሩት ተጫዋቾች ውስጥ ያልመጣችው ተጫዋች ዓባይነሽ ኤርቄሎ ናት። ከቴክኒክ ክፍል አልማዝ ወቅቱ የመስቀል በዓል ስለሆነ ያንን ትቼ አልመጣም በሚል እንደቀረች ነግራኛለች። ለእኔ በቀጥታ መንገር የነበረባት ቢሆንም በአልማዝ በኩል ደርሶኛል። በሷ ደረጃ ከሚገኝ ተጫዋች ይህን ምክንያት ስላልጠበቅኩ አስገርሞኛል።

ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጋር ስላለው መናበብ

ብዙም እንዳንናበብ ያደረገን የሁለታችንም ውድድር በእኩል ጊዜ መምጣት ነው። በእኔ እና አሰልጣኝ ፍሬው መካከል ለመተጋገዝ ጥረት አድርገናል። ከባንክ የመረጣቸው ስድስት ተጫዋቾች ቡድኑን ሳይቀላቀሉ በፊት ኬንያ እኣለን ቡድኑን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው አስረድቻቸው እዚህ እንደገቡ በመላክ አግዤዋለሁ። እሱም የምጠቀምባቸውን ተጫዋቾች በወቅቱ አስረክቦኛል። ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ስለሆነች በርካታ ወጣቶች አሏት፤ እከሌን ልቀቅልኝ የምንኣባልበት ምክንያትም አይኖርም። አሁን እንኳን ቤተልሄም በቀለን ስለቀነስኳት እሱ ጋር ተቀላቅላለች።

የቆመ ኳስ መከላከል

እንደምንናገረው አይደለም። በወንዶችም በሴቶችም በተመሳሳይ የተቆጠርብንም ሆነ እኛ ለማስቆጠር የምንቸገረው ረጃጅም እና የቆሙ ኳሶች ነው። ይህን ለማስተካከል ተነጋግረን በመዘጋጀት እየገባንም ጎሎች ይገቡብን ነበር። ሆኖም በመጨረሻው ጨዋታ ቪሂጋ ክዊንሶች በተደጋጋሚ ሞክረውብን ሊያስቆጥሩብን አልቻሉም ነበር። ምክንያቱም በሒደት የአየር ላይ አጠቃቀማቸውን እና አቋቋማቸውን ማወቅ ጀመርን። ይህን ነገር ለወደፊቱ ማስቆም ባንችል እንኳ ለመቀነስ ሥራዎችን ሰርተናል።

ሎዛ አበራ

ስለ አምበልነቷ እና ኃላፊነት

ከትንሽ ደረጃ በሂደት እሲህ እንደደረሰ ተጫዋች ሀገሬን እና የምጫወትበትን ክለብ በአምበልነት የመምራት አላማ ነበረኝ። ይህን እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። የእግርኳስ ህይወቴን በአግባቡ በመምራቴ ያገኘሁት ነገር ነው። ለዚህም አሰልጣኜን ኃላፊነት አምኖ ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ። ሀገርን መወከል ትልቅ ኃላፊነት ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ደግሞ እስካሁን ያላሰካሁት በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ሙሉ አቅሜን እጠቀማለሁ። ብናገራቸው የሚሰሙ፤ ቢናገሩኝ የምሰማቸው ተጫዋቾች ናቸው በስብስቡ ውስጥ ያሉት። ይህ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ። በተቻለ መጠን አምበል በተጫዋች እና አሰልጣን መካከል ሆኖ ሜዳ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ መስራት ያለበትን ስራ በተለይም የተጫዋቾቹን በማበረታታትና ከሌሎች ስሜቶች ወጥተው ስለማሸነፍ እንዲያስቡ በማድረግ ረገድ ጥረት እያደረግኩ ነው።

ከመዲና ጋር ስላላት ጥምረት

መዲና ቴክኒክ ላይ ጥሩ ናት ። በነፃነት የምትጫወት ናት። ይህ ደግሞ እግርኳስን ቀላል ያደርግልናል። ከዚህ ቀደም ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ላይ አብረን ስለምንተዋወቅ እሷም ምን አይነት አጨዋወት እንዳላት የእኔንም አጨዋወት እንተዋወቃለን። አሁንም ድጋሚ ተገናኝተናል። በተሻለ ሁኔታ ጎሎች ለማስቆጠር እና ለጎል ለማመቻቸት እንጥራለን። በብሔራዊ ቡድን የተሻለ ታሪክ እንደምናስመዘግብ አስባለሁ።

ስለ ዩጋንዳ

የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ቀላል ቡድን አይደለም። አሰልጣኜም እንደተናገረው በመከላከል ላይ አመዝኖ የሚጫወት ቡድን ነው። ጥቅጥቅ ብለው ይጫወታሉ ፤ በራጃጅም እና በቆሙ ኳሶች ለመጠቀም ይሞክራሉ። የእኛ አሰልጣኞች ሲያሰሩን የነበረው ደግሞ በራሳችን ጠንካራ ጎን ላይ ነበር። ‘ያለን አቅም ምንድ ነው ? በምንስ መልኩ ውጤት ማሳካት እንችላለን ?’ በሚለው ላይ ነው እየሰሩን ነው ያሉት። እኔም ጎል አስቆጣሪ እንደመሆኔ መጠን በዚህ ጨዋታም ጎል አስቆጥራለሁ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻቻለሁ። በተቻለ መጠን በደርሶ መልሱ ጨዋታ የተሻለ ውጤት እናመጣለን።