ኢትዮጵያዊያን እንስት ዳኞች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ለመምራት ዛሬ ወደ ዳሬሰላም አምርተዋል፡፡

በ2022 ሞሮኮ ለምታስተናግደው የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በማጣሪያው ከዩጋንዳ ጋር ላለባት ጨዋታ በዛሬው ዕለት የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ወደ ስፍራው የሚያመራ ሲሆን በዳኝነት ደግሞ ዳሬሰላም ላይ ታንዛኒያ ናሚቢያን በሜዳዋ የምታስተናግድበትን ጨዋታ አራት ሴት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ለመምራት ከሰዓታት በፊት ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡

ነገ ማክሰኞ 9፡00 ላይ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም የሚደረገውን ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የከፍተኛ ልምድ ባለቤቷ ሊዲያ ታፈሰ ስትመራው በረዳት ዳኝነት ወይንሸት አበራ እና ብርቱካን ማሞ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ መዳብ ወንድሙ ተመርጠው ተጉዘዋል፡፡

በመሀል ዳኝነት ይህን ጨዋታ የምትመራው ሊዲያ ታፈሰ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገውን የካፍ የሴቶች የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግን ለመዳኘት እና ተጨማሪ ሥልጠናን ለመውሰድ በቀጥታ ወደ ግብፅ ካይሮ እንደምታመራ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡