ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ተጀምሯል። በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 አዲስ የውድድር ዘመን አዲስ ቡድን

በኢትዮጵያ የክለቦች እግርኳስ ውድድር ውስጥ የአጭር ጊዜ እሳቤዎች የገነገነው አስተሳሰብ ስለመሆኑ ይታመናል። ይህም ክለቦች በአጭር በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ በተተለሙ ውጥኖች ከመንቀሳቀስ ይልቅ ለክለቦቹ ዘላቂ ጥቅምን በማያስገኘው የአጭር ጊዜ እሳቤ ውስጥ መሽከርከር የተለመደ ባህል ሆኗል።

የእዚህ አሉታዊ እሳቤ መገለጫም ከዓመት ዓመት የሚለዋወጡ አሰልጣኞች እና የእነሱን ሹም ሽር ተከትሎ የሚታየው የተጫዋቾች የጅምላ ቅያሬ ጉዳይ አንዱ ማሳያ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ጅማሮውን ባደረገው የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ክለቦች ዐምና ከምናውቃቸው በብዙ መንገዶች ተለውጠው ብቅ ብለዋል።

ለውጦችን በአውንታዊ እና አሉታዊ አውድ መመልከት ተገቢ ቢሆንም በአንዳንድ ክለቦች የተመለከትናቸው ለውጦች ግን ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው። በቡድን ስብስብ ረገድ ቡድኖች ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ እንዲሆኑ ባይጠበቅም በጣም በበዛ ቁጥር መለዋወጦች መኖራቸው ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በዝውውር በጥቅሉ ያመጧቸውን ተጫዋቾች እንኳን ትተን ለማሳያነትም ዐምና ይጠቀሙባቸው ከነበሯቸው የመጀመሪያ 11 ተሰላፊ ተጫዋቾች አንፃር እንኳን ስንመለከት ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮችን መታዘብ እንችላለን። በዚህ ረገድ ዐምና ይጠቀምባቸው ከነበሩ የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ የተቀየረን የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎችን ካስመለከተን ጅማ አባጅፋር እና 10 እና ስምንት ተጫዋቾች የለወጡት ሀዲያ ሆሳዕናን እና አዳማ ከተማ እንደ የቅድመ ተከተላቸው ጨምሮ በርካቶቹ ክለቦች አምስት እና ከዚያ በላይ የተጫዋቾች ለውጦችን አደርገዋል።

በተቃራኒው አንድ የተጫዋች ለውጥ ብቻ ያደረገውን ፋሲል ከነማን ጨምሮ ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ የመሳሰሉ ውስን ቡድኖች ቡድናቸው ላይ መጠነኛ ለውጦችን ብቻ በማድረግ ለአዲሱ የውድድር ዘመን ቀርበዋል።

ምናልባት መለዋወጦቹ ታስቦባቸው የተደረጉ ናቸው ብለን እንዳንወስድ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ ቡድኖቹ በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ በርካታ ተጫዋቾች ሲለውጡ የመመልከታችን ጉዳይ የተለመደ እየሆነ ከመምጣቱ አንፃር ይህ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ በየዓመቱ እየፈረሱ የሚገነቡ ቡድኖች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። እጅግ አንገብጋቢ በሆነ የፋይናንስ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የተጫዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል የተቸገሩ ቡድኖች በበዙበት ሊግ በየዓመቱ በዚህ አይነት ሒደት ውስጥ መቀጠላችን ምን ድረስ እንደሚያስጉዘን የምናየው ይሆናል።

👉 አይነተኛ የከፍተኛ ሊግ ባህሪን የተላበሱት መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተካፋይ የነበሩት እና ከየምድባቸው (አርባምንጭ ከተማ ምድብ “ሐ” ያለምንም ሽንፈት እንዲሁም መከላከያ በምድብ “ሀ” በ38 ነጥቦች) የበላይ ሆነው በማጠናቀቅ ወደተናፈቁበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም የሚመልሳቸውን ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ከፕሪምየር ሊጉ አንፃር ፍፁም የተለየ ባህሪ ያለው ውድድር እንደሆነ ይታወቃል። ለባህሪ መለያየቶች የተለያዩ ጉዳዮች በምክንያትነት መቅረብ ቢችሉም ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ወይንም ያለማደግን እጣ የሚወሰንበት ውድድር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቡድኖች ጥንቃቄን መርጠው ስህተቶችን ለመቀነስ ይበልጥ በቀጥተኛ አጨዋወት የሚጫወቱበት በዚህም የተነሳ ለማፈትለክም ሆነ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ኳሶችን ለማሸነፍ ከፍ ያለ የአካል ብቃት ዝግጁነት የሚጠይቅ ውድድር እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ከጥቂት በልዩነት ከሚነሱ ቡድኖች ውጭ አብዛኞቹ ቡድኖች ስሪታቸው ከላይ ያነሳናቸውን ሀሳቦች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተሻለ ጥራት መከወን በሚያስችል አወቃቀር ይገነባሉ።

ታድያ ሁለቱን ቡድኖች ዳግም በመጀመሪያ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያገናኘው ጨዋታ አይነተኛ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ይመስል እንደነበር መመልከት ይቻላል። ሁለቱም ቡድኖች ኳሱን ሲያገኙ በፍጥነት ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን ሲጥሉ የተመለከትንበት፣ በርከት ያሉ የአንድ ለአንድ የአየር ላይ ግንኙነቶች የበዙበት፣ በርከት ያሉ አካላዊ ፍትጊያዎችን የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።

ምንም እንኳን ጨዋታው በመከላከያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም የሁለቱ ቡድኖች እና ከፍ ያለ የአካል ብቃትን የተመለከትንበተ ጨዋታ ሆኖ አልፏል። እርግጥ በእግርኳስ የማሸነፍያ የሚባል አንድ መንገድ ባይኖሩም ቡድኖቹ በሊጉ በሚኖራቸው ቀጣይ ቆይታዎች በምን መልኩ ራሳቸውን ከሊጉ የጨዋታ መንገድ ጋር ያስማማሉ ወይንስ ቀጥተኝነታቸውን በላቀ የጥራት ደረጃ በመከወን የሊጉ ክለቦችን ምቾት በመንሳት ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 አሸናፊዎቹ ካቆሙበት ቀጥለዋል

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ፋሲል ከነማዎች ፍቃዱ ዓለሙ ደምቆ በዋለበት ጨዋታ አዲሱን የውድድር ዘመን ሀዲያ ሆሳዕናን 3-1 በመርታት ዐምና ካቆሙበት ቀጥለዋል።

“በእግርኳስ ዋንጫዎችን ከማሸነፍ ይልቅ ክብሮችን ማስጠበቅ ከባዱ ፈተና ነው” የሚል ለእውነታነት የቀረበ አባባልን ልብ ላለ ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እና ቡድናቸው ይህን ክብር ለማስጠበቅ ከፍ ያለ ፈተና ዘንድሮ ከተቀናቃኞቻቸው እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።

ፋሲል ከነማዎች በስብስብ ደረጃ ወሳኝ አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም እና የቀኝ መስመር ተከላካያቸው እንየው ካሣሁንን ቢያጡም ከሁለቱ ተጫዋቾች ጋር በተመጣጣኝ ደረጃ በሚገኙ ተጫዋቾች ከመተካት ባለፈ ብዙ አማራጭ የሚሰጣቸውን አስቻለው ታመነን ወደ ስብስባቸው ቀላቅሏል። ይህም ቡድን በብዙ ሳይነካካ ባለበት ለመቀጠል የሚያስችለው ነው።

ከዋንጫ በኋላ የሚኖረው የውድድር ዘመን ቡድኖች በዋነኝነት የሚፈተኑባቸው ጉዳዮች መካከል ተጫዋቾች ላይ ተመሳሳይ የድል ረሀብ ስሜትን ለመፍጠር መቸገር እንዲሁም ተጋጣሚዎች የቡድኑን የአሸናፊነት ምስጢር የነበረውን የጨዋታ መንገድ በመረዳት እና ለዚህ ማምከኛ የሚሆኑ አማራጭ የጨዋታ መንገዶችን ይዘው በመቅረባቸው እና በሌሎች ምክንያቶች ክብርን የማስጠበቅ ሒደቱ ፈተና ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል። ፋሲሎችም ይህን ፈተና በምን መልኩ ሊወጡት ይችላሉ የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

በመጀመሪያው ጨዋታ የተመለከትነው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ተስፋ የሚሰጥ ነበር። በተሻለ መነቃቃት ጨዋታውን ያደረጉት የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች በዘንድሮው የውድድር ዘመን አምና ይጠቀሙበት ከነበረው የተጫዋቾች አደራደር በተለየ በሶስት የኋላ ተከላካዮችን መነሻ ባደረገ አዲስ የተጫዋቾች አደራደር እና የጨዋታ አቀራረብን ለመተግበር ጥረት አድርገዋል። እንዲሁም ሙጂብ ቃሲምን ያጣው ቡድኑ ኦኪኪ አፎላቢ ባልተሰለፈበት ጨዋታ ፍቃዱ ዓለሙ ሐት-ትሪክ በመሥራት ለቡድኑ ሌላ የግብ አማራጭ ሆኖ ብቅ ማለትን ጨምረን በጥቅሉ ስንመለከት አስቀድመን ለዘረዘርናቸው ስጋቶች ቡድኑ አማራጭ መንገዶችን ይዞ እየመጣ እንደሆነ አጀማመራቸው ፍንጭ የሚሰጥ ይመስላል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና ያለ አቡበከር ናስር

ዐምና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ኢትዮጵያ ቡና ከማጠናቀቁ በስተጀርባ የወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለፅ አልነበረም። 29 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ የአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ባጠናቀቀት 2013 አቡበከር ኢትዮጵያ ቡናን ተሸክሞ ለሁለተኝነት አብቅቷል ብንለው ለተፅኖው የሚያንስ አይሆንም።

ታድያ አቡበከር ናስር በሜዳ ውስጥ መኖሩ ለኢትዮጵያ ቡና በእንቅስቃሴ ረገድ የሚሰጠውን የሜዳ ላይ ጥቅም እንኳን ወደ ጎን ትተን አቡበከር በቡድን ዝርዝር ውስጥ መኖሩ ብቻ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች የልብ ልብን የሚሰጥ መሆኑን መታዘብ ችለናል። ከአምና የውድድር ዘመን በተንከባለለ የአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ሲገጥሙ አቡበከር ናስርን መጠቀም ያልቻሉት ቡናዎች በብዙ መንገዶች ተቸግረው እንደነበር መታዘብ ችለናል።

አቡበከር ናስር በሜዳ ላይ ከሚያስቆጥራቸው ወሳኝ ግቦች ባለፈ ለቡድኑ አጋሮቹ የራስ መተማመንን በመስጠት፣ ቡድኑን በመምራት እና በማበረታት ብሎም የቡድኑ አጠቃላይ የመከላከል ሆነ የማጥቃት መዋቅር ላይ ወሳኙ መዘውር እንደሆነ እና የሲዳማ ቡናው ጨዋታ ህይወት ያለ አቡበከር ናስር ለኢትዮጵያ ቡና ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የታዘብንበት ነበር።

አቡበከር ናስር ገና በለጋ እድሜው ከእድሜ እርከን ቡድኖች በቀጥታ በመምጣት የቡድኑ ብዙ ነገር ለመሆን በቅቷል። መሰል ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያላቸውን ተጫዋቾች በስበስብ ውስጥ መያዝ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ ሆኖ ቡድኖች ግን በእነዚህ ተጫዋቾች ላይ ያለ ልክ ጥገኛ የሚሆኑ ከሆነ እነዚሁ ተጫዋቾች በማይኖሩባቸው ጊዜያት አጠቃላይ የቡድኑ መዋቅር እንዲፋለስ በማድረግ ቡድኖች ሲቸገሩ ይስተዋላል። በመሆኑም አሰልጣኝ ካሣዬም አቡበከር በተለያዩ ምክንያቶች የማይኖርባቸው ጊዜያትን ታሳቢ በማድረግ አማራጮችን የማይፈልጉ ከሆነ አይበለውና ተጫዋቾቹ በተለያዩ ምክንያቶች በሜዳ ላይ በማይኖርባቸው ቀናት ፍፁም የተዳከመውን ቡና የመመልከታችን ነገር የሚቀር አይመስልም።

👉 በትልቅ ደረጃ ለመፎካከር የቆረጠ የሚመስለው ባህር ዳር ከተማ

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ባህርዳር ከተማዎች እርግጥ ገና የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ላይ ብንገኝም በእጃቸው ከያዙት ስብስብ እና የውድድር ዘመኑን የጀመሩበት መንገድ መነሻነት ከወዲሁ ከፍ ባለ ደረጃ ለመፎካከር የሚያስችል አንዳች ነገር እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶችን እየተመለከትን እንገኛለን።

በፕሪምየር ሊጉ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ ከዓመት ዓመት በመሻሻል ሒደት ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያደረጉት የአሰልጣኝ ቅጥር እና የተጫዋቾች ምልመላ በእራሱ ቡድኑ ጠንካራ እና አሸናፊ ቡድን ወደ መሆን ላስቀመጠው ውጥን መሳካት የቡድኑን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል። በንፅፅር የተሻለውን ስብስብ የያዙት አሰልጣኝ አብርሃምም ይህን ስብስብ በምን መልኩ አቀናጅተው ውጤት ያስመዘግባሉ የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ።

በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት አዲስ አዳጊውን አዲስአበባ ከተማን ገጥመው 3-0 ማሸነፍ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች ገና የመጀመሪያ ጨዋታ ቢሆንም በሒደት የቡድኑ አባላት ከጉዳት የሚርቁ ከሆነ እና ይበልጥ ቡድኑ እየተዋሀደ ሲመጣ ቡድኑ ከአሁኑ ይበልጥ የተሻለ አስፈሪ ቡድን የመሆን እድሉ ሰፊ መሆኑን ተከትሎ መጪው ጊዜ ለባህርዳር ከተማ ከወዲሁ ብሩህ ይመስላል።

👉 ለሀዲያ ሆሳዕና መልክ መቀየር ምልክት የሰጠው ውጤት

ቡድኖች የሚከተሉት የጨዋታ ዘይቤ ከዓመት ዓመት በወጥነት ሲቀጥል መገለጫቸው ይሆናል። ተጫዋች ሲገዙ፣ አሰልጣኝ ሲቀጥሩ፣ የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች ሲያቋቁሙ እና ሌሎች ለውጦችን ሲያደርጉም መገለጫቸው የሆነውን አጨዋወት መሰረት አድርገው ይቀጥላሉ። ይህ ጤናማ አካሄድ በሀገራችን ህልም ነው ማለት ይቻላል። በአንድ የውድድር ዓመት የአንድ ቡድን ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የነበረው ነጥብ በቀጣዩ እጅግ ደካማ ጎኑ ሆኖ ሲመጣ ይታያል። ይህ መሆኑ በጊዜው ያሉ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ላይ ጣት እንዲጠቆም መነሻ ቢሆንም ጊዜ የሚያስፈልገው የቡድን ግንባታ ሂደት በጤናማ አስተዳደር ካልታጀበ ተመሳሳይ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር መሆኑ ይዘነጋል።

ሀዲያ ሆሳዕናን ለዚህ እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ሀዲያ አምና በሊጉ 26 ግቦችን ብቻ አስቆጥሯል። በዚህ ረገድ ቡድኑ የሚበልጠው የመጨረሻ ደረጃን ይዘው የጨረሱት አራት ቡድኖች ብቻ ነበር። ይህ እጅግ ደካማ ቁጥር ቢሆንም ቡድኑ አራተኛ ደረጃን ይዞ እንዲጨርስ ምክንያት የሆነው በፋሲል ከነማ ብቻ የተበለጠው የመከላከል ቁጥሩ ነበር። በዓመቱ 19 ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ ሳይሆን አመዛኞቹ ጎሎች የተቆጠሩበትም በመጨረሻ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ተጫዋቾቹን ባጣባቸው ጨዋታዎች መሆኑ ለመከላከል ጥንካሬው ሌላ ማስረጃ ነበር።

ዘንድሮ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክለብ አዲስ አሰልጣኝ እና አዲስ ስብስብ ይዞ ውድድሩን የጀመረው ሆሳዕና ገና በመጀመሪያው ግጥሚያ ሦስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ይህንን ላየ በጥሩ ሁኔታ ለተጀመረው አንዳች መገለጫ ለነበረው የቡድኑ ባህሪ መለወጥ በየዓመቱ የምናየው ስር ነቀል የቡድን ምስረታ አባዜ ምክንያት መሆኑን ማሰብ ቀላል ነው። አዲሱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በአዲሱ ስብሳቸው ወደሚፈልጉት የጨዋታ አፈፃፀም ለመድረስ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው። ነገር ግን ለክለቡ ጥሩ መሰረት ያያዘ የመሰለው የአምናውን ቡድን እሴት ማስቀጠል እጅግ ከባድ እንደሚሆንም እርግጥ ሆኗል። ሆሳዕናም ጥቂት ግቦች ከተስተናገደባቸው ቡድኖች መደዳ የመሰለፉ ነገር ከወዲሁ አጠያያቂ ሆኗል።