የኢትዮጽያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አዲስ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሾሟል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአስገዳጅ ምክንያት አዲስ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሾሟል።

ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴካፋ ከ20 በታች የሴቶች ውድድር ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ቦታውን በአሰልጣኝ የነበረው ፀጋዘአብ አስገዶም ሸፍኖ የነበረ ቢሆንም ለውድድሩ በክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ፈቃድ አለማግኘቱን ተከትሎ በምትኩ በግብጠባቂነት እና በግብጠባቂ አሰልጣኝነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያሳለፈው ቅጣው ሙሉን አዲሱ የብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኞች ስብስብ አባል አድርጓል።

ዓምና በኢኮሥኮ የሰሩት አሰልጣኝ ቅጣው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ቡድን ግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ እንደነበሩ አይዘነጋም።