ኢትዮጵያ ቡና አዲስ የቡድን መሪ አግኝቷል

የመዲናው ክለብ በማስታወቂያ አወዳድሮ አዲስ የቡድን መሪ ማግኘቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለዋናው የወንዶች ስብስቡ የቡድን መሪ ለመቅጠር መስከረም 30 በሪፖርተር ጋዜጣ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወቃል። ክለቡ በጋዜጣው ባወጣው ማስታወቂያ በርካቶች የተወዳደሩ ሲሆን አቶ ሙሉጌታ አስፋው ማሸነፋቸውም ታውቋል።

ክለቡ ያወጣውን የትምህርት ደረጃ እና የሥራ ልምድ እንዳሟሉ የተገለፀው አቶ ሙሉጌታ አስፋው በማኒጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ የተቀበሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መድን፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፤ ሰበታ ከተማ እና መከላከያ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወጣት፤ የኦሊምፒክ እና የዋናው ብሔራዊ ቡድን በእግርኳስ ተጫዋችንት ማሳለፋቸው ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዞረውን ኢኮሥኮን በቡድን መሪነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።