ሉሲዎቹ ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

ነገ 10 ሰዓት ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ሉሲዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ዛሬ አከናውነዋል።

ሞሮኮ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ የጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከአምስት ቀናት በፊት ወደ ካምፓላ አምርቶ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከዩጋንዳ አቻው ጋር አድርጎ ሁለት ለባዶ መሸነፉ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ከተመለሰ በኋላ ማረፊያውን በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በማድረግ ለመልሱ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን ሲያደርግ ነበር። በዛሬው ዕለትም ስብስቡ ከረፋዱ 4:30 ጀምሮ ለ65 ደቂቃዎች የዘለቀ ልምምዱን ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ሰርቷል።

ቀለል ያሉ ሥራዎች በተከናወኑበት የቡድኑ የዛሬ የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አስተውለናል። በቅድሚያ ተጫዋቾቹ የማፍታታት ስራዎችን ከከወኑ በኋላ በሁለት ቡድን ተከፋፍለው ከኳስ ጋር ቀለል ያለ የቅብብል ሥራዎችን እንዲሰሩ ተደርጓል። በመጨረሻ ደግሞ በነገው ጨዋታ የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡ ተጫዋቾች የቆመ ኳስ እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ልምምድ የሰሩ ሲሆን አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ተጫዋቾቹን ታክቲካዊ ንድፈ ሀሳብ ከመጀመሪያው ጨዋታ መነሻነት ሲያስረዱ አይተናል። ምክትል አሠልጣኟ ሰርካዲስ እውነቱ በበኩሏ ሌላኛውን ቡድን መሐል ባልገባ ይዘት ያለው ልምምድ ስታሰራ አስተውለናል።

በትናንትናው ዕለት የኮቪድ-19 ምርመራ ያደረጉት የቡድኑ አባላትም በተመሳሳይ ነገ ጨዋታ በሚያደርጉበት የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ትናንት ረፋድ ላይ ልምምድ ሰርተው ነበር። የኢትዮጵያ እና የዩጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ነገ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።