“እግርኳስን በማያውቁ ሰዎች የተወሰነብኝ ውሳኔ ከእግርኳሱ አያርቀኝም ” – አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር

አዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ አሰልጣኝ እስማኤል አበቡበከርን ከኃላፊነታቸው ማሰናበቱን ተከትሎ አሰልጣኙ በዚህ መልኩ ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታ እና ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

” ይህ ውሳኔ ዛሬ የተወሰነ አይደለም። ለስድስት ወር ያህል ታቅዶበት ሴራ ሲጎነጎን ቆይቶ እና ተቀነባብሮ የተወሰነ ውሳኔ ነው። አስቀድሜ ይህ እንደሚመጣ አውቅ ነበር። ምክንያቱም እግርኳሱ ላይ ሊበሉ ያሰፈሰፉ ሰዎችን እንደምከላከል ስለሚታወቅ ነው። እኔ የምባረረው ‘ወይ አይበላ ወይ አያስበላ’ ተብዬ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ። ስለዚህ የተነሳሁበት ምክንያት ዋናው ይሄ ነው።

”ሌላው የዲሲፕሊን ኮሚቴው የወሰነው ፕሮፌሽናል ያልሆነ፥ ያልሰለጠነ እና ገለልተኛ ያልሆነ ውሳኔ ነው። ገለልተኝነቱም የሚያጠራጥር ነው። ምክንያቱም ሁሉም አካላት ማለትም ስራ አስኪያጁ፥ ቡድን መሪው፥ ዲሲፕሊን ኮሚቴውም ሆነ ሌሎቹ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ሠራተኞች ናቸው። ስለዚህ ገለልተኝነቱን እጠራጠራለው። በአዲስ አበባ ክለብ ውስጥ ያለፉትን አራት ዓመት ሥሰራ ምንም አይነት ጥፋት አልተገኘብኝም ነበር። እነዚህ ሰዎችም በቦታው አልነበሩም። እንደዚህ አይነት ጥፋት ተጠፍቷል ቢባል እንኳን የመጀመርያ ማስጠንቀቂያ ሊሰጡኝ ይገባ ነበር። ይህ ሳይሆን ቀጥታ ይባበር ብሎ መፃፍ ከዲሲፕሊን መርህ አንፃር ተገቢ አይደለም። በአጠቃላይ ውሳኔው አግባብነት የሌለው፥ ወገኝተንተኝነት ያለበት እና የአንድ ወገንን የበላይነት የታየበት በመሆኑ የማልቀበለው ነው። ቡድን መሪው እኔን ለማሸማቀቅ የተጠቀመበትን ቃል አጥንተው እንኳን ውሳኔ አልሰጡም። ምክንያቱም አስቀድመው ያሴሩት እቅዳቸው ስለነበረ ነው።

”ያም ሆኖ እግርኳስን በማውያቁ ሰዎች የተወሰነብኝ ውሳኔ እኔን ከእግርኳሱ አያርቀኝም፤ በዚህ አጋጣሚ ለቡድኑ ተጫዋቾች ያለኝን አክብሮት እየገለፅኩ በሚችሉት አቅም ሁሉ አዲስ አበባን በዚህ ዓመት በሊጉ እንዲቆይ ጠንክረው በርትተው እንዲስሩ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።”


የክለቡ የስንብት ደብዳቤ