“ትልቅ ድል ነው እንደ ሀገርም ፣ እንደ አሰልጣኝም” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ቻምፒዮን በመሆን የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ስለ ውድድሩ ተከታዩን አስተያየት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ዩጋንዳ አቅንቶ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ የውድድሩ ሻምፒዮን በመሆን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሴቶች እግርኳስ ታሪክ ስኬታማ ውጤት አስመዝግቧል። ለቡድኑ ውጤት ማማር ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱ የቡድኑ አባላት መካከል የሆኑት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ስለውድድሩ አጠቃላይ ሁኔታ ተከታዩን አስተያየት አጋርተውናል።

ስለ ውድድሩ

“ከመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች አንስቶ እስከመጨረሻው ከባድ ነበር። ውድድሩ እንደሚታወቀው አንድ ቀን እያረፍክ የምትጫወተው ነው። በማናውቀው ሀገር እና በማናውቀው አየር እንዲሁም አመጋገብ ይሄን ሁሉ ተቋቁመው ነው ሴት እህቶቻችን ይህንን ውጤት ያመጡት፤ ስለዚህ ሊመሰገኑ ይገባል። እንደ ሴት ልጅ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመዋል። ወደ ዳኝነቱ መምጣት አያስፈልግም። የነበረው ነገር ትንሽ ሚዛናዊ አልነበረም። እሱን ሁሉ ተቋቁመን ነው ይሄ ዋንጫ የመጣው።”

ከሁለት ለባዶ ከመመራት እና በጊዜ የቁጥር ብልጫ ተወስዶበት አሸናፊ ስለመሆናቸው

“የመጣውን ትልቁን ነገር ያደረገው አምላክ ነው። ሁለት ለባዶ እየተመራን እነሱ መከላከልን መረጡ። በቁጥር ብልጫ አላቸው፤ ሆኖም በማጥቃት እኛን እንደማይችሉ ስለገባኝ ተከላካይ ቀንሼ አጥቂዎቹን 4 አደረግኳቸው። እግርኳስ አንዳንዴ ሁለት ለባዶም ተሸነፍክ ሦስት ለባዶ ያው ነው። ብዙዓየሁ ታደሰን አስወጥተን አርየትን ነው ያስገባነው፤ ማጥቃት እንዳለብን እና ውጤተቱን መቀየር እንደምንችል ስላመንን። ያው እንዳያችሁት ለጎሎቹም መቆጠር የእርሷ አስተዋጽኦ ነበር። ሲቀጥል በቁጥር በልጠው መከላከላቸው ይበልጥ ጠቅሞናል። ትልቅ ድል ነው እንደ ሀገር፣ እንደ አሰልጣኝ፣ እንደ ተጫዋቾቸም በጣም በጣም ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው። ለመነቃቃቱም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ ።”

ድሉ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ስለሚኖረው አስተዋፅኦ

“እንግዲህ እንዲህ ነው ብለህ የምትገምተው ነገር ባይሆንም የእግርኳስ ስፖርት ሂደት ነው። አሁንም ብዙ ፕሮሰሶች አሉ። ከባድ ነው፤ ወደ ላይም ሄጄ ተጫዋች ማምጣት አልችልም፤ ወደታችም እንደዛው። እሱም አንድ ፈተና ስለሆነ አሁን ከፊታችን ከቦትስዋና ጋር ጨዋታ አለብን። እርሱ ላይ የተስተካከሉ ተጫዋቾችን እና የተሻለ ቡድን ሰርተን ለመቅረብ እንሞክራለን። ከዚህ በኋላ ጨዋታዎች እየጠነከሩ ነው የሚሄዱብን። ምክንያቱም የምስራቅ አፍሪካ ቻምፒዮን እንደሆንን ስለሚያውቁ ጠንክረውብን ነው የሚመጡት።”