ንግድ ባንክ ለዕድሜ እርከን ቡድኖቹ አሠልጣኞች ሾሟል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ መልክ ላቋቋማቸው የእድሜ እርከን ቡድኖች ዋና አሠልጣኞች ቀጥሯል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም የነበረው ባንክ ከአራት ዓመታት በፊት የወንዶች ቡድኖቹን ማፍረሱ ይታወሳል። ከወራት በፊት ግን ዋናውን የወንዶች ቡድን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከሚወዳደረው ኢኮሥኮ በመረከብ ዳግም ወደ እንቅስቃሴ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖቹን ወደ ውድድር ለማስገባት አሠልጣኞችን መሾሙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ20 ዓመት በታች ዋና አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው ዕድሉ ደረጄ ነው። የቀድሞ የአየር መንገድ፣ ባንኮች፣ ኢትዮጵያ ቡና እና መድን ተጫዋች የነበረው እድሉ እግርኳስን ካቆመ በኋላ የኢትዮጵያ ቡና ወጣት ቡድንን እና ዋናውን ቡድን (በጊዜያዊነት) ማሰልጠኑ ይታወሳል። ከዛም በአንደኛ ሊግ በወቅቱ የሚሳተፈውን ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በዋና አሠልጣኝነት መርቶ ነበር። እድሉ ከደብረብርሃን ዋና አሠልጣኝነቱ ከተነሳ በኋላ ዘለግ ላሉ ጊዜያት በአሠልጣኝነት ሳንመለከተው ብንቆይም የተለያዩ ሥልጠናዎችን እና ትምህርቶችን ሲወስድ በመቆየት አሁን በተጫዋችነት ያሳለፈበት እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያሳካበት ባንክን ለማሰልጠን የአንድ ዓመት ፊርማውን አኑሯል።

የክለቡ ከ17 ዓመት በታች አሠልጣኝ የሆነው ደግሞ ታዲዮስ ተክሉ ነው። ወጣቱ አሠልጣኝ ታዲዮስ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን የዕድሜ እርከን ቡድኖች ማሰልጠኑ ይታወሳል። እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሴቶች ቡድን ውስጥ በረዳትነት ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ደግሞ እንደ ዕድሉ ሁሉ ከ20 በላይ አመልካች አሠልጣኞችን በመብለጥ በተመሳሳይ የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።