ከፍተኛ ሊግ | ሀምበሪቾ ዱራሜ አዳዲስ በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀምበሪቾ ዱራሜ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮችንም ውል አራዝሟል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ መሪነት በምድቡ የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት ከጫፍ ደርሶ የነበረው ክለቡ ለ2014 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙን በመሾም ጅምሩን ያደረገ ሲሆን በመቀጠል በቅርቡ በለገጣፎ አብሮት መስራት የቻለው መላኩ ከበደ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ክለቡን በተጫዋችነት ያገለገለው ብሩክ ሲሳይን በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን ሦስት ወጣት ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ ወደ አስራ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አስፈርሞ የስምንት ነባሮችን ውል አራዝሟል፡፡

ክለቡን ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል ክለቡን ከዚህ ቀደም ማገልገል የቻለውና በሀድያ ሆሳዕና፣ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ በአዳማ ከተማ ያሳለፈው የመስመር ተከላካዩ ትዕግስቱ አበራ፣ የቀድሞው የጅማ አባቡና ፣ መድን እና የቤንች ማጂ ቡናው ተከላካይ ሂደር ሙስጠፋ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ሲጫወት የነበረው ምንያምር ጴጥሮስ፣ በደደቢት እንዲሁም ባለፈው ዓመት በወልድያ ያሳለፈው ዳግማዊ ዓባይ፣ ከዚህ ቀደም በዲላ ከተማ ፣ ስሑል ሽረ ፣ ደቡብ ፓሊስ እና ሀላባ በመጫወት ያሳለፈው አማካዩ ኪዳኔ አሰፋ ፣ በኢትዮጵያ ቡና እና ዐምና በአዳማ ከተማ በመጫወት ያሳለፈው አጥቂው ሰይፈ ዛኪር፣ በድሬዳዋ ከተማ እና ባለፈው ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የደመቀው አጥቂው ዘርአይ ገብረስላሴ ይጠቀሳሉ።

ከላይ ከተጠቀሱት በቀጨማሪ አንተነህ ሀብቴ (ግብ ጠባቂ ከደሴ ከተማ)፣ ምንታምር መለሰ (ግብ ጠባቂ ከሺንሺቶ ከተማ)፣ ስንታየው አሸብር (አማካይ ከአርባምንጭ)፣ በሱፍቃድ ነጋሽ (አማካይ ከለገጣፎ)፣ አቤል ዘውዱ (አማካይ ከደብረብርሃን)፣ ዮናስ ሰለሞን (አማካይ ከአዲስ አበባ ከተማ)፣ በድሉ መርዕድ (አማካይ ከደሴ ከተማ)፣ የኃላሸት ፍቃዱ (አጥቂ ከአዳማ ከተማ)፣ ልዑልሰገድ አሰፋ (አጥቂ ከደሴ ከተማ) ሲፈርሙ ወጣቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች እና ባለፈው ዓመት በዱራሜ ከተማ በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ጥሩ ጊዜ የነበረው ፅዮን ዘለቀ እንዲሁም ከዱራሜ ከተማ አጥቂው ኃይለየሱስ ዓለሙ እና አማካዩ እንዳሻው ጫሚሶ አዲሶቹ የአሰልጣኝ ዳዊት ፈራሚዎች ናቸው፡፡

ክለቡ ከአዳዲሶቹ ተጫዋቾች ባለፈ የእንዳለ ዮሀንስ ፣ ታሪኩ ታደለ ፣ ታዬ ወርቁ ፣ ሙሉነህ ገብረመድህን ፣ ምናሴ በራቱ ፣ ተመስገን አሰፋ ፣ አላዛር አድማሱ እና እሸቱ አጪሶን ውል በማራዘም ከዱራሜ ከተማ ወደ ባቱ በመዞር ዝግጅቱን መስራቱን ቀጥሏል፡፡