የከፍተኛ ሊግ ውድድር የጅማሮ ቀን ተራዘመ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን የጅማሮ ቀን ተገፍቷል፡፡

በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የ2014 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ቀደም ብሎ ፌዴሬሽኑ የዕጣ ማውጣቱ ቀን ኅዳር 5 እንዲሁም የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ኅዳር 20 ቀን 2014 መሆኑ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ ገልፆ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባልተገለፀ ምክንያት የዕጣ ማውጣቱ እና የጅማሮው ቀን ላይ ማሻሻያ አድርጎበታል፡፡ በዚህም መሠረት ኅዳር 15 የዕጣ ማውጣቱ እና የደንብ ውይይቱ የሚካሄድ ሲሆን ውድድሩ የሚጀመርበትን ቀን በአንፃሩ ኅዳር 25 ቀን 2014 እንዲሆን ማድረጉን ድረ ገፃችን ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ተብሎ የነበረው የዝውውር ቀነ ገደብ እስከ ኅዳር 10 እንዲሆን በድጋሚ የተራዘመ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮኖች ላይም የቀን ሽግሽግ ሊያደርግ እንደሚችል ሰምተናል፡፡