የ2014 ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጥቅምት ወር የሶከር ኢትዮጵያ ምርጦች

የዘንድሮው የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሦስት ሳምንት ጨዋታዎች ተካሂደዋል። በ36ቱ ጨዋታዎች ላይ በመመስረትም እንደተለመደው በ30% የአንባቢያን እና በ70% የድረ-ገፃችን ባልደረቦች ድምፅ ተከታዮቹን የወሩ ምርጦች በኮከብነት ሰይመናል።

የወሩ ኮከብ ተጫዋች – ሀብታሙ ተከስተ (ፋሲል ከነማ)

ከእስከዛሬ የወሩ ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ውድድር የዐፄዎቹ አማካይ በአንድ ነጥብ ብልጫ አሸናፊ ሆኗል። ተጫዋቹ በተደረጉት ሦስት ጨዋታዎች (ከሀዲያ ሆሳዕና ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር) ላይ ወጥ አቋም አሳይቷል። በተለይም ፋሲል በተፈተነበት የወልቂጤ ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፍ ወሳኟን ጎል ያስገኘችውን ኳስ ማመቻቸት ችሏል። ሀብታሙ ከተከላካይ መስመር ፊት በሚሰጠው የተለመደው ኃላፊነት የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ጨዋታን በማንበብ በማቋረጥ እና ስኬታማ ሸርተቴዎችን በመከወን ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል። ከዚህ በተለየ ተጫዋቹ እያሳየ ባለው ሌላኛው መልክ የቡድኑን የማጥቃት ሂደት በማስጀመር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ታይቷል። ከእስካሁኑ በተለየ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ቀርቦ የመጫወት ዓይነት ኃላፊነት ሲሰጠውም በማጥቃት እንቅስቃሴው ውስጥ የነበረው ተሳትፎ የሚና ሽግሽጉን በአግባቡ እንደተገበረ የሚያሳይ ነበር። ድረ-ገፃችን በየጨዋታ ሳምንቱ በምትመርጠው የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥም ሁለት ጊዜ የመካተቱን ዕድል አግኝቶ ነበር።

ሀብታሙ ተከስተ ከአንባቢያን በተሰብሰበው ድምፅ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አጠቃላይ የነጥብ ድምሩ 69.6 ሆኖ አንደኛ ተመራጭ ሆኗል። በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ 68.6 ድምር በመያዝ በዛብህ መለዮ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የአንባቢያን ቀዳሚ ምርጫ የሆነው ሀይደር ሸረፋ በ61.2 ድምር በሦስተኝነት አጠናቋል።

የወሩ ኮከብ አሠልጣኝ – ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በሦስቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን በማሳካት ቡድናቸውን በሰንጠረዡ አናት አስቀምጠዋል። ከድሉ ባሻገር ቡድናቸው ከቻምፒዮንነት ቀጥሎ ባለው ፈታኝ ዓመት የድል ርሀቡ ሳይረግብ እንዲቀጥል ማድረግ ችለዋል። በጨዋታ ዕቅድ እና የአሰላለፍ ምርጫም በቀላሉ ተገማች ያልሆኑ እንዲሁም የተጨዋቾችን ብቃትም ከግምት ያስገቡ አቀራረቦችን በመተግበር ስኬታማ ሆነዋል።


አሠልጣኝ ሥዩም በአንባቢያንም ሆነ በሶከር ኢትዮጵያ ባልደረቦች ድምፅ አሸናፊ በመሆን በ100 ነጥቦች በሰፊ ርቀት አንደኛ ሆነዋል። በመቀጠል የባህር ዳር ከተማው አሠልጣኝ አብርሀም መብራቱ በ54.6 እንዲሁም የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ደግሞ በ49.6 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃውች ይዘው አጠናቀዋል።