አዲስ አበባ ከተማ ቅጣት ሲተላለፍበት ቡድን መሪውም ታግደዋል

አዲስ አበባ ከተማ በፈፀመው የዲሲፕሊን ጥሰት የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት የክለቡ ቡድን መሪውም የስድስት ወራት የዕግድ ውሳኔ ተላለፈባቸው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሁለተኛ ጊዜ ያደገው እና በአሰልጣኙ እና በቡድን መሪው መካከል በተፈጠረ ያለመግባባት ከዋና አሰልጣኙ እስማኤል አቡበከር ጋር የተለያየው የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ከአሰልጣኙ ስንብት በኋላ በረዳት አሰልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር መከላከያን 3ለ0 በሆነ ውጤት መርታቱ ይታወሳል፡፡ ክለቡ ጨዋታውን ድል ካደረገ በኋላ የመከላከያ ክለብ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሁለት ቢጫ (በቀይ) ካርድ የወጣን ተጫዋች ክለቡ አሰልፎ ተገኝቷል በማለት ያቀረበውን ጥቆማ ሲከታተል የነበረው የሊግ ካምፓኒው የዲሲፕሊን ኮሚቴ አዲስ አበባ ከተማን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

በዚህም መሠረት አዲስ አበባ ከተማ በ2013 በተደረገው የከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተወገደውንና አንድ ጨዋታ የታገደው ኢያሱ ለገሰን ማከሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ ም ክለቡ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው የ 1 ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ አስመዝገቦ ስለማጫወቱ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ለማረጋገጥ ችሏል። ስለሆነም አዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቹ አንድ ጨዋታ ማረፍ ሲገባው ይህ ባለመሆኑ ለፈፀመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል ሁለት አንቀፅ 36 (ሐ) መሰረት ክለቡ ሃያ ሺህ ብር እንዲቀጣና በዕለቱ የክለቡ የቡድን መሪ የነበረው ሲሳይ ተረፈ ለስድስት ወራት እንዲታገድ ተወስኗል።

 

በተጨማሪም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል ሁለት በአንቀጽ 36 ሸ እና ና 46 ሐ መሰረት ከላይ በባህርዳር እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ላይ የተላለፉት ውሳኔዎች በሙሉ አንዲፀኑ ወስኗል።