የትልቁን ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ ትመራዋለች

በግብፅ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘውን የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የሀገራችን እንስት ዳኛ እንደምትመራው ታውቋል።

ስምንት የክፍለ አህጉሩ የእንስቶች የሊግ አሸናፊ ክለቦች የየዞናቸው መሪ ሆነው በግብፅ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ እየተካፈሉ እንደነበር ይታወሳል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገውን ውድድር ለመምራት 12 ዳኛች መመረጣቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነርሱም ውስጥ ኢትዮጵያዊቷ የመሐል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ትገኛለች። በሞሮኮው ኤፍኤአር ራባት (አርሚ ሮያል ራባት) እና በናይጄሪያው ሪቨርስ ኤንጅልስ መካከል የተደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ ከማላዊ፣ ኬንያ እና ቶጎ ረዳቶቿ ጋር በመሆን በጥሩ ሁኔታ የመራችው ሊዲያ ከዛም በኋላ በአራተኛ ዳኝነት አንድ ጨዋታ አከናውናለች። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ካፍ የፍፃሜውን ጨዋታ እንድትመራ ሊዲያን መርጧታል።

በነገው ዕለት በጋናው ሀሳካስ ሌዲስ እና በደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ መካከል የሚደረገውን የፍፃሜ ጨዋታ ሊዲያ ከመስመር ዳኞቹ ኩዊንሲ ኩሎዲያ ቪክቶሪ (ሞሪታኒያ) እና ሚሚሲን አጋታ ኢዮሬ (ናይጄሪያ) እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛዋ ሳሄንዳ ሳድ ሳድ ዓሊ ኤልማግሀረቢ (ግብፅ) ጋር በመሆን እንደምትመራው ታውቋል። ይህንን ተጠባቂ የፍፃሜ ጨዋታ ሊዲያ ነገ ከመራች በኋላ ቅዳሜ ጠዋት ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመለስም ይጠበቃል።