ከፍተኛ ሊግ | ኢትዮጵያ መድን አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም በርከት ያሉ ወጣቶችንም አሳደጓል

የቀድሞው አሰልጣኙ በፀሎት ልዑልሰገድን ከወር በፊት የሾመው ኢትዮጵያ መድን የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅሞ የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራትም በማራዘም እና ታዳጊዎችን በማሳደግ ወደ ዝግጅት ገብቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚወዳደረው አንጋፋው ኢትዮጵያ መድን በተጠናቀቀው የውድድር አመት ያጣውን ወደ ፕሪምየር ሊግ የመመለስ ተስፋውን ዘንድሮ ለማሳካት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ላይ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ብርቱ ፉክክር ለማድረግ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ የቀድሞው አሰልጣኙ በፀሎት ልዑልሰገድን በድጋሚ ከወር በፊት መቅጠር የቻለው ክለቡ አስራ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ሲያስፈርም የአምስት ነባሮችን ኮንትራት በማራዘም ስድስት ወጣት ተጫዋቾችን ደግሞ ከቢ እና ከሲ ቡድኑ ወደ ዋናው አሳድጓል፡፡

ጆርጅ ደስታ በድጋሚ ወደ ቀድሞው ክለቡ ተመልሷል፡፡ ከሙገር ሲሚንቶ የተገኘው እና መድንን ከለቀቀ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ቆይታን ማድረግ ችሎ የነበረው ግብ ጠባቂው በድጋሚ ወደ ቀደመው ክለቡ መመለስ ችሏል፡፡ የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በወልድያ ሲጫወት የነበረው አጥቂው ያሬድ ዳርዛን ጨምሮ አብርሀም ከተማ (ግብ ጠባቂ ከለገጣፎ ለገዳዲ)፣ ተስፋዬ ታምራት (ተከላካይ ከኢኮሥኮ)፣ ቻላቸው መብራቱ (አማካይ ከነቀምት ከተማ)፣ አሚር ሙሰዲር (አማካይ ከገላን)፣ ፀጋ ዓለማየሁ (ተከላካይ ከገላን)፣ ሳምሶን ደረጀ (አማካይ ከወላይታ ሶዶ)፣ ሀይከን ድዋሞ (አማካይ ከወልድያ)፣ በረከት ራህመት (አጥቂ ከሞጆ ከተማ) እና እዮብ ገብረማርያም (አጥቂ ከወሎ ኮምቦልቻ) የክለቡ አዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነው ተቀላቅለዋል፡፡

ዳንኤል ይስሀቅ (ግብ ጠባቂ)፣ ሚፍታህ አወል (ተከላካይ) ፣ በኃይሉ ሀይለማርያም (አማካይ) ፣ ጌትነት ተስፋዬ (አማካይ) ፣ ያሬድ ካህሳይ (ተከላካይ) ውል ያራዘሙ ነባር ተጫዋቾች ሲሆኑ ተጫዋቾችን በማሳደግ የሚታወቀው ክለቡ ከታችኛው ቡድኑ ሲሳይ ማስረሻ፣ አብዱልከሪም አረቦ፣ መስፍን ዋሴ፣ mሐመድ ኑር፣ ይትባረክ ሰጠኝ፣ አሸናፊ ተስፋዬ እና ሰልሀዲን አብደላ የተባሉ ስድስት ወጣቶችን ማሳደጉን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡