አንድ ተጫዋች ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጭ ሆናለች

የካፍ የልህቀት ማዕከል ከቀናት በፊት ዝግጅቱን የጀመረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አንድ ተጫዋች ከስብስቡ ውጭ ማድረጉ ታውቋል።

በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሀያ ሁለት ተጫዋቾችን በመጥራት ከቀናት በፊት አያት በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት አንድ ተጫዋች ከስብስቡ ውጭ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በቅርቡ ንግድ ባንክን የተቀላቀለችው ዮርዳኖስ ምዑዝ ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ የሆነች ተጫዋች ስትሆን ምክንያቱ ደግሞ የፖስፖርት ጉዳይ አለመሟላቱን ተከትሎ እንደሆነ ሰምተናል። በእርሷ ምትክ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ተጨማሪ ተጫዋች በቀናት ውስጥ በስብስብስባቸው ውስጥ እንደሚያካትቱ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና የመጀመርያ ልምምዳቸው ቀን የአሠልጣኝ ቡድን አባል የሆኑት የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ቅጣው ሙሉ ያልነበሩ ሲሆን አሁን ቡድኑን በመቀላቀል መደበኛ ልምምዳቸውን ሲከውኑ በስፍራው በመገኘት ተመልክተናል። በጥሩ መንፈስ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ የመለማመጃ ሜዳው ምቹ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ፌዴሬሽኑ ሌሎች የተሻሉ አማራጭ ሜዳዎችን መፈለግ ትኩረት ሰጥቶት ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ታዝበናል።