አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ተፋጠዋል

በአንድ ተጫዋች ይገባኛል አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ዘገባችን የአዲስ አበባ ከተማው ተከላካይ ኢያሱ ለገሠ በቅድመ ስምምነት ጅማ አባ ጅፋርን ለመቀላቀል ተስማምቶ በቢሸፍቱ ከተማ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት ሲሰራ ቢቆይም የኋላ ኋላ አዲስ አበባ ከተማ ”ከኔ ጋር እስከ ጥቅምት 30 ድረስ የሚያቆየው ኮንትራት ያለው በመሆኑ ወደ ቡድኔ ይመለስ” በማለት በሊጉ የሦስት ሳምንት ጨዋታዎችን በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት ሲያገለግል ቆይቷል።

ጥቅምት 30 ኮንትራቱ ማለቁን ተከትሎ አዲስ አበባዎች የኢያሱን ውል ለተጨማሪ ዓመታት ለማራዘም ወደ ፌዴሬሽን ቢሄዱም ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ ውሉን ሳያራዝሙ ቆይተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ”ቅድመ ስምምነት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የፈፀምክ በመሆንህ ህጋዊነትህ ለጅማ አባ ጅፋር ነው” በማለት።

ተጫዋቹ ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ከተማ የመቆየት ፍላጎት ያለው ቢሆንም ጅማ አባ ጅፋሮች በገባው ስምምነት መሠረት ወደ ክለቡ መጥቶ መጫወት እንዳለበት እየገለፁ ይገኛል። የዚህ ውዝግብ መቋጫ የሚሰጠው የእግርኳሱ የበላይ አካል ፌዴሬሽኑ ከውሳኔ አስቀድሞ በሁለቱ ክለቦች መካከል መግባባት በመፍጠር ጉዳያቸውን እንዲፈቱ ጥቆማ ሰጥቷል። ሆኖም ግን ሁለቱ ክለቦች ስምምነት የማይደርሱ ከሆነ ፌዴሬሽኑ በህጉ መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ የሚወስን ይሆናል።

ዛሬ ከሰዓት አዲስ አባበ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ኢያሱ ለገሰ የማይሰለፍ መሆኑን አረጋግጠናል።