ተስፈኛው አማካይ ወደ ጅማ አባ ጅፋር አቅንቷል

በኢትዮጵያ ቡና የማደግ ዕድል ያልተሰጠው ወጣቱ አማካይ ጅማ አባ ጅፋርን መቀላቀሉ ተረጋግጧል።

በአስኮ ፕሮጀክት ያደገው እና ያለፉትን አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ከአስራ ሰባት ዓመት በታች አንስቶ በተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ሙሴ ከበላ ዘንድሮ ከዋናው ቡድን ጋር ሲሰራ ቢቆይም እድል አለማግኘቱን ተከትሎ በደንቡ መሠረት በቢጫ ቴሴራ ወደ ጅማ አባ ጅፋር የሚያደርገው ዝውውር ተጠናቋል።

በብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ምክንያት ሊጉ በመቋረጡ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አንዳንድ ወጣቶችን ወደ ሀዋሳ በመጥራት የሙከራ ጊዜ እየሰጡ ሲገኝ ሙሴ ከበላ የዚህ አካል በመሆን ባደረገው መልካም እንቅስቃሴ አሰልጣኙን በማሳመኑ ከኢትዮጵያ ቡና መልቀቂያ በመውሰድ ለአንድ ዓመት ፊርማውን አኑሯል። ዛሬ በአራተኛ ሳምንት ጅማ አባጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በሚኖረው ጨዋታ አሰልጣኝ አሸናፊ በአሰላለፋቸው ውስጥ አካተው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ይጠበቃል።

በ2013 መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ቡና በስካይ ላይት ሆቴል ባደረገው የኮከቦች ምርጫ ሙሴ ከበላ ከተስፋ ቡድኑ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ከመመረጡ ባሻገር ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወቱ ይታወቃል።