ከፍተኛ ሊግ | ቡታጅራ ከተማ ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮችን ውልም አድሷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ስር ሲወዳደር የቆየው ቡታጅራ ከተማ አዳዲስ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስራ ስድስት ነባሮችን ውልም አድሷል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል አንዱ በምድብ ሐ የሚገኘው ቡታጅራ ከተማ አንዱ ነው፡፡ ከአሰልጣኝ ካሊድ መሀመድ ጋር ከተለያየ በኋላ በምትኩ የቀድሞው አሰልጣኙን መሳይ በየነን የተካው ክለቡ ለ2014 የሊጉ ውድድር ጠንክሮ ለመቅረብ ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች አስፈርሟል፡፡

ወሰኑ ዓሊ የቡታጅራ ከተማ ቀዳሚ ፈራሚው ሆኗል፡፡ ባህርዳር ከተማን ረዘም ላሉ ዓመታት በማገልገል የሚታወቀው የፊት መስመር ተጫዋቹ በኢትዮጵያ መድን ካሳደጉት አሰልጣኝ መሳይ ጋር አብሮ ለመስራት ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡የቀድሞው የወላይታ ድቻ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በደሴ ከተማ በአማካይ ስፍራ ሲጫወት የምናውቀው አማካዩ ዮሴፍ ድንገቶም ሌላው ፈራሚ ነው።

መሳይ ሰለሞን (አጥቂ ከገላን ከተማ)፣ እንዳለማው ታደሰ (አጥቂ ከደሴ ከተማ)፣ ሄኖክ ባንጃው (አማካይ ከመድን)፣ አስተዋይ በዛብህ (ተከላካይ ከፌደራል ፖሊስ)፣ ሰይፈ መገርሳ (ተከላካይ ከፌዴራል ፓሊስ)፣ ማሩፍ መሐመድ (ተከላካይ ከአርሲ ነገሌ) እና ምኞት ሲሳይ (ግብ ጠባቂ ከቂርቆስ ክ/ከተማ) ሌሎች የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡፡

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በክለቡ መቀመጫ ከተማ ቡድኑ ከጀመረ የሰነባበተ ሲሆን ወደ አስራ ስድስት በክለቡ የነበሩ ተጫዋቾች ውል ለተጨማሪ ዓመት እንደታደሰላቸው ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው ዝርዝር መረጃ አመላክቷል፡፡