ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የ4ኛ ሳምንት የተጫዋቾች ትኩረት ደግሞ ተከታዩቹ ሀሳብ ተዳሰውበታል።

👉 ታታሪው ሀቢብ ከማል

አምና በሁለተኛው ዙር ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለቆ ወደ ሌላኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ወደ ነበረው እና በአሰልጣኝ መሀመድኑር ንማ የሚመራው ኮልፌ ቀራንዮ አምርቶ በፍጥነት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን የበቃው አማካዮ ሀቢብ ከማል በክረምቱ የዝውውር ወደ አርባምንጭ ከተማ ያደረገውን ዝውውር ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ መልካም የሚባል አጀማመርን እያደረገ ይገኛል።

ወጣቱ አማካይ አምና በከፍተኛ ሊጉ ለኮልፌ ቀራንዮ 6 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ዘንድሮም በከፍተኛ ሊጉ ከኮልፌ ቀራንዮ ጋር አንድ ምድብ ወደ ነበረው አርባምንጭ ከተማ ካመራ ወዲህ ቡድን በመጀመሪያ ተመራጭነት እያገለገለ ይገኛል። በጣም ታታሪ እንዲሁም ጠንካራ ምቶች ባለቤት የሆነው ሀቢብ በፍጥነት ራሱን ከፕሪሚየር ሊጉ ጋር እያስተካከለ ይገኛል።

አርባምንጭ ከተማዎች ባህርዳር ከተማን 2-1 በረቱበት ጨዋታ ድንቅ የጨዋታ ቀንን ማሳለፍ የቻለው አማካዩ የባህርዳር አማካዮች በነፃነት ኳስ እንዳይቀበሉ ከፍተኛ ጫናን በማሳደር መጫወት ለፈለገው ቡድኑ ከፍተኛ ግልጋሎትን የሰጠ ሲሆን ከዚህ ባለፈ በጨዋታው በስድስት አጋጣሚዎች ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ጠንካራ ሙከራዎችን ሲያደርግ አስተውለናል።

ከዚህም ባለፈ ቡድኑን አቻ ያደረገችውን አስደናቂ የቅጣት ምት ኳስ በግሩም ሁኔታም ማስቆጠር ችሏል። ወጣቱ አማካይ እያሳየ የሚገኘውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል ይበልጥ ራሱን ለማሳደግ ታትሮ መስራቱን የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ ይበልጥ ከፍ ባለ ደረጃ የምንመለከተው ይሆናል።

👉 ገና በሙከራ ላይ የሚገኘው የወልቂጤ የአጥቂ መስመር

አራተኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ በደረሰው አዲሱ የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ድላቸውን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ያሳኩት ወልቂጤ ከተማዎች ከውጤቱ ባሻገር አሁንም ያላቸውን የአጥቂ ተጫዋቾች አማራጮች በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል መዋቅር ለማግኘት ሙከራ እያደረጉ ይገኛል።

በእስካሁኑ አራት የሊግ ጨዋታዎች ቡድኑ አራት የተለያዩ የፊት መስመር የተጫዋቾች ጥምረቶችን ተመልክተናል። ከጥምረቶቹም ባለፈ ተጫዋቾቹን በመጠኑም ቢሆን ከጨዋታ ጨዋታ የሚቀያየር በሚመስል ሚና ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉም ተስተውሏል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በእስካሁኑ የሊግ ጨዋታዎች ከተጠቀሟቸው ተጫዋቾች መነሻነት በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ባህሪያቸው የሚለያይ ቢሆንም ሦስት በዘጠኝ ቁጥር ሚና መጫወት የሚችሉ አጥቂዎች (ጌታነህ ከበደ ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ አህመድ ሁሴን) እንዲሁም ሁለት በመስመር አጥቂ/አማካይነት/ መጫወት የሚችሉት ጫላ ተሺታ እና ያሬድ ታደሰ በድምሩ አምስት አጥቂዎች በእጃቸው ላይ ይገኛሉ።

በመጀመሪያው ጨዋታ ቡድኑ ሦስቱን የፊት አጥቂዎችን በአንድ ላይ (እስራኤል-ጌታነህ-አህመድ) አሰልፎ ለመጠቀም ሲሞክር አስተውለናል ፤ በሁለተኛ እና በሦስተኛው ጨዋታ ደግሞ ጌታነህን ከያሬድ እና ጫላ እንዲሁም ከአህመድ እና ጫላ ጋር በጣምራ የተጠቀሙ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ለ4-4-2 ዳይመንድ(4-1-3-2) የተጫዋቾች አደራደር ፊት ላይ ጌታነህ እና እስራኤል በአጥቂነት እንዲሁም ከእነሱ ጀርባ በመጀመሪያው አጋማሽ ያሬድ ታደሰን በሁለተኛው ደግሞ አብዱልከሪም ወርቁን በአስር ቁጥር ሚና ለመጠቀም መሞከራቸውን አስተውለናል።

ከጥምረቶቹ መለዋወጥ ባለፈ ቡድኑ በአራት ጨዋታ ከያዘው የአጥቂዎቹ ጥራት አንፃር ያስቆጠረው የግብ ብዛት ሦስት መሆኑ የአጥቂ መስመሩ አሁንም ገና ብዙ የሚቀረው ጉዳይ እንዳለ ማሳያ ነው። የአጥቂዎች ውህደት በአንድ ጀምበር ይፈጠራል ተብሎ ባይጠበቅም ቡድኑ በአንዱ ጥምረት ረግቶ ተደጋጋሚ የጨዋታ ጊዜ መስጠቱ ግን አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል።

በመጀመሪያው ጥምረት ላይ ሦስቱንም የፊት አጥቂዎች ለመጠቀም በሞከሩበት ጨዋታ ላይ በመሀል አጥቂነት የጀመረው ጌታነህ ከበደ ይበልጥ ወደ ኋላ እየተሳበ እንደ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር እንዲጫወት በማድረግ ይበልጥ ደግሞ አህመድ እና እስራኤል ጌታነህ ወደ ኋላ በመሳቡ ክፍት የሚሆነውን ሳጥን ከውጪ ወደ ውስጥ ሩጫዎችን እንዲያደረጉ ሳጥኑን እንዲያጠቁ ኃላፊነት እንዲወስዱ መደረጉ በወረቀት ላይ የተሻለው አማራጭ ይመስላል።

በሁለተኛ እና ሦስተኛው ጨዋታ ላይ ቡድኑ ጌታነህን በመጨረሻ አጥቂነት እንዲሁም ከእሱ ግራ እና ቀኝ ፈጣን የሆኑትን አህመድ /ጫላ /ያሬድን ለመጠቀም ጥረት ለማድረግ ሞክሯል በእነዚህም ጥምረቶች ወቅት በተለይ ከአህመድ ሁሴን ውጪ የተቀሩት ተጫዋቾች ኳሱን ስለሚፈልጉ ይበልጥ ወደ መሀል የመሳብ እና እንቅስቃሴ ላይ የማተኮር ሂደት ጎልቶ ተስተውሏል።

በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት ጌታነህ እና እስራኤል ከፊት እንዲሁም ከእነሱ ኋላ ካሉት ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮችን ለመጠቀም ጥረት ያደረገው ቡድኑ ምንም እንኳን ጨዋታውን ቢያሸንፍም አሁንም የአጥቂ መስመሩ በሚፈለገው ልክ የሰመረ አልነበረም።

በእነዚህ ሁሉ ጥምረቶች ውስጥ አሰልጣኙም በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ወቅት ሲነገሩ እንደተደመጠው የጌታነህ ከበደን ወደ ኋላ ተሳትፎ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ የመሆን እና ኳሶችን ይዞ የመግባት አቅሙን ለመጠቀም ፍላጎት እንዳለ ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን ከጌታነህ ጋር የሚጣመሩት ተጫዋቾች ማንነት እና ከእሱ እንቅስቃሴ ጋር የማናበብ (Synchronize) የማድረጉ ሥራ ግን እስካሁን መፍትሔ የተገኘለት አይመስልም።

👉 ሁሉን ያሟላው ሚሊዮን ሰለሞን

ገና አራተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በሚገኘው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መልካም የሚባል የውድድር ዘመን አጀማመር እያደረጉ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል የአዳማ ከተማው ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን አንዱ ነው።

አምና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ሲዳማ ቡናን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ያመራው ወጣቱ ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን እንደ ቡድን ደካማ ጊዜያትን ባሳለፈው አዳማ ውስጥ ወጣ ገባ የነበረ የውድድር ዘመን ማሳለፉ ይታወሳል።

ዘንድሮ ግን በስብስብ ጥራት ከፍ ብሎ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመራ በሚገኘው የአዳማ ከተማ ቡድን ውስጥ ጥሩ የሚባል አጀማመር እያደረገ ይገኛል። በእስካሁኑ የአራት ጨዋታ ጉዞ አንድ ጎልን ማስቆጠር የቻለው ሚሊዮን በመስመር ተከላካይነት ሆነ በመሀል ተከላካይነት ድንቅ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል።

በቀኝ የመስመር ተከለካይነት በጀመረባቸው ጨዋታዎች አስደናቂ የማጥቃት ተሳትፎን የሚያሳየው ተጫዋቹ ወደ ኋላ ተመልሶም የሚያሳው የመከላከል አበርክቶ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተመሳሳይ ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ አቻ ሲለያይ በመጀመሪያ አጋማሽ ከቶማስ ስምረቱ ጋር ተጣምሮ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ቡድኑ ወደ ኋላ ሦስት ተከላካይ በተቀየረበት ወቅት ከሦስቱ የመሀል ተከላካይ ውስጥ የግራውን ተከላካይ በመሆን ጥሩ እንቅስቃሴን አሳይቷል።

እርግጥ ሆሳዕናዎች ብዙም የተቀናጀ የማጥቃት እንቅስቃሴን ባንመለከትባቸውም በቦታ ሽግሽግ የመሀል ተከላካይ ሆኖ የተጫወተው ሚሊዮን ሰለሞን በመሀል ተከላካይነትም ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሌላ አማራጭ መሆን እንደሚችል ያስመሰከረበት የጨዋታ ዕለት ነበር።

👉 ኢያሱ ታምሩ በቋሚ ተሰላፊነት

የመጀመሪያ ተሰላፊነት እግርኳስን ፍለጋ ኢትዮጵያ ቡናን የለቀቀው እያሱ ታምሩ በሀዲያ ሆሳዕና ቤት ይህን በሚገባ እያሳካ ይመስላል። ከመስመር አማካይነት በሂደት ወደ መስመር ተከላካይነት የተቀየረው ተጫዋቹ በሀዲያ ሆሳዕና ቤት በግራ የመስመር ተከላካይነት እያገለገለ ይገኛል።

በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፓፖዲች መልማይነት በ2007 ክረምት የኢትዮጵያ ቡና “አብዮት” አካል በመሆን ከከፍተኛ ሊግ ክለብ ሀላባ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራው እያሱ ታምሩ በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ከሞላ ጎደል በቋሚ ተሰላፊነት ቡድኑን በሚገባ ያለው ሳይሰስት አገልግሏል። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ መምጣትን ተከትሎ ግን በተመራጭነት ዝርዝር ውስጥ የኋለኛው ተርታ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።

በመሆኑም በክረምቱ በኢትዮጵያ ቡና የነበረው የውል ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ያመራው እያሱ ታምሩ ከእንቅስቃሴ ርቆ የቆየ ቢሆንም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ዳግም ተመልሶ በአዲሱ ክለቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል። በቀጣይ የቡድኑ አምበል የሆነው እና ጉዳት ላይ የሚገኘው የቦታው ተሰላፊ ሄኖክ አርፌጮ ወደ ሜዳ ሲመለስ እያሱ ቦታውን ለማስከበር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃዋል።

👉 ከቆይታ በኋላ ተፅዕኖ የፈጠረው ሪችሞንድ አዶንጎ

በ2011 የውድድር ዘመን በወልዋሎ ዓ/ዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ያስተዋወቀው ግዙፉ ጋናዊ አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ በመጀመሪያው የውድድር ዘመን ቆይታው በቢጫው መለያ ተስፋ ሰጪ ነገር ማሳየት ቢችልም ከዛ ወዲህ ግን ተፅዕኖው በጣም ቀንሶ እየተመለከትነው ነበር።

ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በድሬዳዋ ከተማ ቆይታን ያደረገው ሪችሞንድ አምና እስከ 23ኛው ሳምንት ድረስ ግብ ሳያስቆጥር መዝለቁ በብዙ ሲያስተቸው የነበረ ጉዳይ እንደነበረ አይዘነጋም። በ23ኛው ሳምንት ወልቂጤን ሲረቱ ሁለት እንዲሁም በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ፋሲል ከነማ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሮ የውድድር ዘመኑን በሦስት ግቦች ማጠናቀቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በክረምቱ ወደ አዲስአበባ ከተማ ዝውውሩን ሲያደርግ በርካቶች በግርምት ቅንድባቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ያስገደደ ነበር። ብዙዎች ዝውውሩን ጥያቄ ውስጥ እንዲከቱም ያስገደደ ነበር።

በአዲሱ ክለቡ ባደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ፍፁም ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረገው ሪችሞንድ በአራተኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ፋሲል ከነማን 2-1 ሲረቱ ከጊዜያት በኋላ በበጎ ተፅዕኖ የፈጠረበት ጨዋታ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።

የመጀመሪያውን ግብ ለአዲስአበባ ማስቆጠር የቻለው ሪችሞንድ ኤልያስ አህመድ ላስቆጠራት ኳስም አመቻችቶ በማቀበል ድንቅ የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል። ከግቦች ተሳትፎ ባለፈ በጨዋታው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለበት ቀን ነበር።

ብዙ ተጠብቆበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣው ሪችሞንድ በቀጣይ ጨዋታዎችም የቡድኑን ተጫዋቾች ከፊት ሆኖ በመምራት የመዲናዋ ክለብ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ዓይነተኛ ሚና መወጣት ይገባዋል።

👉 ባለ ሐት-ትሪኩ ማማዱ ሲዲቤ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ሀገራችን ከመጡ የውጪ ሀገር ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች የሚመደበው ማማዱ ሲዲቤ በአዲሱ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን ሦስታ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ላይ መስራት ችሏል።

በመጀመሪያዎቹ 35 ደቂቃዎች ግቦቹን ማስቆጠር የቻለው ተጫዋቹ ሁለቱ ኳሶች ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ከተሻሙ የቅጣት ምት ኳሶች ያስቆጠረ ሲሆን አንደኛው ኳስ እንዲሁ ከቀኝ መስመር ከተሻገረ ኳስ የተገኘች ነበረች።

ከመስመር እየተነሳ እንዲሁም በመጨረሻ አጥቂነት መጫወት የሚችለው ሁለገቡ አጥቂ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ካመራ ወዲህ እስካሁን አራት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ማማዱ ሲዲቤ ባለፉት ዓመታት ከኢታሙና ኬይሙኒ (በመጀመሪያው ቆይታ) እና ሀብታሙ ወልዴ በኋላ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ለተቸገሩት ድሬዳዋ ከተማዎች አጥጋቢ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የቃልኪዳን ዘላለም ደስታ አገላለፅ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በወላይታ ድቻ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 ሲረታ ግብ አስቆጥሮ ያሳየው የደስታ አገላገለፅ አስገራሚ ነበር።

በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲየ ጎሜስ ስር በኢትዮጵያ ቡና በተለይ በ2011 የውድድር ዘመን ከታኛው ቡድን አድጎ ዕምነት ተጥሎበት ገና በለጋ ዕድሜው በትላልቅ ጨዋታዎች ሳይቀር የመሰለፍ እድልን አግኝቶ የነበረው ቃልኪዳን ዘላለም ከኢትዮጵያ ቡና ከተለያየ ወዲህ በደደቢት ፣ በሰበታ ከተማ እንዲሁም ዘንድሮ ደግሞ በወላይታ ድቻ ቤት ቆይታን እያደረገ ይገኛል።

ወጣቱ አጥቂ በሰበታ ቆይታው ተቀይሮ ገብቶ በቀደሞው ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ላይ የማስተዛዘኛ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በድቻ መለያ የመክፈቻዋን ግብ በቡና መረብ ላይ አሳርፏል። ከግቡ በኋላ ግን ተጫዋቹ ከኢትዮጵያ ቡና በለቀቀበት መንገድ አልያም በሌላ ጉዳይ ደስተኛ እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ የአዲሱን ክለቡን ባጅ እያሳየ በቀድሞው ደጋፊዎቹ ፊት ደስታውን ሲገልፅ ተመልክተናል።