አሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 አዲስ አበባ ከተማ

በመጨረሻዎቹ ደቂቃ በተቆጠሩ ግቦች በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

በጨዋታው ይዘውት ስለገቡት ስልት

“በመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም ቅጣት ምት እስኪሰጥብን ድረስ በፈለግነው መንገድ ተንቀሳቅሰናል። እስከ መጨረሻው ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰን በስተመጨረሻም ግብ አግኝተናል። እንደነበረን እንቅስቃሴ ማሸነፍ ይገባን ነበር።”

ከአሸናፊነት ስለመራቃቸው

“ተጫዋቾቼ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ጫና ውስጥ ስለነበሩ ቀላል ስህተቶችን ይሰሩ ነበር። ከጨዋታ ጨዋታ ራሳችን አሻሽለን ለመቅረብ እንሞክራለን እንደቡድን ግብ የማስቆጠር ችግር አለብን ይህን ማስተካከል ይጠበቅብናል።”

መጨረሻ ላይ ስለተቆጠረችው ግብ

“ቡድናችን እስከመጨረሻው ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል፤ ተጫዋቾቼ በጣም ለፍተዋል። በረኛቸው ብዙ ኳሶችን አድኖብናል። ዛሬ ቀናችን አልነበረም ማለት ይቻላል። ነገርግን ተጫዋቾቼ ባሳዩት ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ሰለጨዋታው

“ኳስ ነው ሁሌ ማሸነፍ የለም። ነገርግን ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል።”

እድሎችን መጠቀም ስላለመቻላቸው

“የተፈጠሩ እድሎች ነበሩ ነገርግን መጠቀም አልቻልንም ፤ ኳስ ላይ የሚፈጠር ሰለሆነ እንቀበለዋለን።”

ስለቋሚ አሰልጣኝነት?

“እናንተ ስላነሳችሁት እንጂ እኔ ጨዋታ አልቆጥርም። ስራ ስለሆነ የተሰጠኝን ሀላፊነት ለመወጣት እጥራለሁ። የዛሬው ሦስተኛ ጨዋታ ነበር፤ ውጤቱ የተመለከታችሁት ነው። የሚመለከተው አካል ውሳኔ ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ።”

ስለቡድኑ መሻሻል

“ከዚህ በፊትም እንደተናገርኩት የኳስ ክህሎት ያላቸው ወጣት ተጫዋቾች አሉ። ከሲቲ ካፑ አንስቶ የነበረን ጊዜ አጭር ነበር። ኳስ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ሂደት ነው፤ ይህን ለማሟላት ጊዜ ወስዷል። የእረፍት ጊዜው የተሰጠንን ጊዜ ተጠቅመን ቡድናችንን ለማሻሻል አግዞናል።”