ኢትዮጵያዊያን እንስት ዳኞች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ዳኞች የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ለመምራት ወደ ዩጋንዳ ያቀናሉ፡፡

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የ2022 የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችንን ሲከውኑ የሰነበቱ ሲሆን ወደ ሦስተኛው ዙር ያለፉ ሀገራትም በዚህኛው ሳምንት ወሳኝ መርሐ-ግብራቸውን ያደርጋሉ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከነገ በስቲያ ቦትስዋናን ከሜዳዋ ውጪ የምትገጥም ሲሆን አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞችም የፊታችን ዕረብ ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ካምፓላ በሚገኘው ሴንት ሜሪ ስታዲየም ዩጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታን በመሀል ዳኝነት የሚመሩ ይሆናል።

በዚህም ፀሀይነሽ አበበ የዚህ ዓመት ሁለተኛ ጨዋታዋን የምትመራ ሲሆን በተደጋጋሚ በማጣሪያ እና በሴካፋ ዋንጫ ሀገራችንን ወክለው ሲዳኙ የነበሩት ወይንሸት አበራ እና ይልፋሸዋ አየለ በረዳትነት መዳብ ወንድሙ በአራተኛ ዳኝነት ይህን ጨዋታ ለመምራት ዛሬ 6፡00 ሰዓት ላይ ወደ ስፍራው አምርተዋል።