ሲዳማ ቡና የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት በአራት ተጫዋቾች ላይም ውሳኔ ተሰጥቷል

በአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በተፈፀሙ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአምስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ተደርገው ከትላንት በስቲያ መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚህኛው የውድድር ሳምንት በተደረጉ ስምንት መርሀግብሮች ላይ በታዩ የክለብ እና የተጫዋቾች የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ስነ ስርአት እና አመራር ኮሚቴ በአንድ ክለብ እና አራት ቀይ ካርድ ተመልክተው በነበሩ ተጫዋቾች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃን ወስዷል፡፡

በዚህም መሠረት ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አድርጎት በነበረው የ5ኛው ሳምንት ግንኙነታቸው የክለቡ ደጋፊዎች በጨዋታው ወቅት እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የእለቱን ዳኛ እና 4ኛ ዳኛውን በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቦበታል። የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ሲዳማ ቡና ሰባ አምስት ሺህ እንዲከፍል ቅጣት ተጥሎበታል።

ሀዋሳ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ያለ ግብ አጠናቆ በነበረው ጨዋታ ሆን ብለህ የተጋጣሚ ተጫዋች ረግጠሀል ተብሎ በቀይ ካርድ ተወግዶ የነበረው ተከላካዩ ፀጋ ሰው ድማሙ የአራት ጨወታ ዕገዳ እና የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡ ፋሲል ከነማ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዶ የነበረው የፋሲሉ አምበል ያሬድ ባዬ የአንድ ጨዋታ ቅጣት ሲጣልበት በዚሁ ጨዋታ ላይ የአርባምንጩን አምበል ወርቅይታደስ አበበን በክርን ተማቶ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ የነበረው አማካዩ ሀብታሙ ተከስተ ለፈፀመው ጥፋት የአራት ጨዋታ ዕገዳ እና የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት በተመሳሳይ በዚህኛው ጨዋታ ላይ የአርባምንጩ አማካይ አሸናፊ ፊዳ የተጋጣሚ ተጫዋች ጎትተሀል ተብሎ ከሜዳ ተወግዶ እንደነበር የሚወሳ ሲሆን የአራት ጨዋታ ዕገዳ እና የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

በሌላ ቅጣት ሀዋሳ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ያለ ግብ ባጠናቀቁት ጨዋታ ላይ የሀዋሳ ተጫዋቾች አምስት ቢጫ ካርድ ስለተመለከቱ ኮሚቴው ክለቡ አምስት ሺህ ብር እንዲከፍል የገንዘብ ቅጣት ጥሎበታል፡፡