ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

የነገ ምሽቱን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተለው ተመልክተናል።

አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በነገው ሁለተኛ መርሐ ግብር ይገናኛሉ። ዕኩል ስምንት ነጥቦች የሰበሰቡት ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሰንጠረዡ ጫፍ የሚያስጠጋቸውን ዕድል ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙ መሆኑ ሲታሰብ ፉክክሩ በጉጉት እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

ከውጤት አንፃር በጥሩ የሥነ ልቦና ደረጃ ላይ ሆነው እንደሚገናኙ የሚጠበቁት ወልቂጤ እና አርባምንጭ ቡድናቸው ውስጥ አሁንም መሻሻሎችን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ሁለት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገበት ወልቂጤዎች ከአጀማመራቸው ቀና ማለት ችለዋል። ያም ሆኖ ጨዋታዎቹን በጠባብ ውጤቶች መደብደማቸው እና ውጤት ለማስጠበቅ ጫና ውስጥ ሲገቡ የታዩባቸው ቅፅበቶች መኖራቸው ቡድኑ አሁንም የአሸናፊነት መንፈሱን ይበልጥ ማሳደግ እንዳለበት ይጠቁማሉ። አርባምንጭ ከተማዎችም በሽንፈት በጀመሩት ውድድር ውስጥ መነቃቃትን እያሳዩ ይገኛሉ። ቡድኑ በየጨዋታው ግቦችን እያስተናገደ መምጣቱን ስናስተዋል ግን ነጥብ ይዞ ለመውጣት በቻለባቸው ጨዋታዎች እንኳን ብዙ ትግል እንዳደረገ መገንዘብ እንችላለን። ከዚህ አንፃር ግቦችን እንደልብ የማያገኙ እና የያዙትን ውጤት አሳልፈው ላለመስጠት ሲጥሩ የሰነበቱ ቡድኖች ጨዋታ አድርገን ልንወስደው እንችላለን።

የነገ ተጋጣሚዎች የአጨዋወት ምርጫ ልዩነት ፉክክሩን መልካም ሊያደርገው ይችላል። ምንም እንኳን ሁለቱም የ 4-4-2 ተጠቃሚ ሆነው ብንመለከትም አርባምንጭ የዝርግ አማካይ ወልቂጤ ደግሞ የዳይመንድ ቅርፅ ያለው አማካይ ክፍልን ምርጫቸው አድርገዋል። በአመዛኙ ጫና ፈጥሮ ኳስ መቀበል እና ፈጥኖ ወደ ፊት ለመድረስ መሞከር የአርባምንጮች መገለጫ ሲሆን ነገም የኳስ ቁጥጥሩ ወደ ወልቂጤዎች ሊያደላ እንደሚችል ይታሰባል። ነገር ግን በድሬዳዋው ድላቸው ላይ ወልቂጤዎች መሀል ለመሀል በቅብብሎች ላይ ተመስርተው የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚሞክሩባቸው አጋጣሚዎች አጥጋቢ አለመሆን ለአርባምጭ ኳስ የመቀማት ጫና እጅ እንዳይሰጡ ያሰጋቸዋል። በዚህ ረገድ እነርሱም አልፎ አልፎ የሚታይባቸው የመልሶ ማጥቃት ባህሪ እና ከመስመር የሚያሻግሯቸው ኳሶች ሊረዷቸው ይችላሉ። ወደ መሀል በጠበበው የቡድኑ የአሰላለፍ ምርጫ በመስመሩ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና የሚኖራቸው የመስመር ተከላካዮቻቸው ከአርባንጭ የቦታው አማካዮች ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶችም ጨዋታውን የመወስን አቅም ሊኖራቸው ይችላል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ያለግብ ጨዋታን የማጠናቀቅ ጉዳይ ዋና ፈተናው ይመስላል። ከቆሙ ኳሶችም ከጨዋታም ግብ እያገኘ ካለ ተጋጣሚ ጋር እንደመገናኘቱም እንደቡድን ያለውን የመከላከል ቅንጅት ፊት ላይ ኳስ በማስጣል ብቻ ሳይሆን ከኋላ ክፍተት ባለመፍጠርም መድገም ይጠበቅበታል። ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት በኩልም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለው የቅብብል ስኬት በነገው ጨዋታ ተሻሽሎ ሊቀርብ የሚገባው ሌላው ደካማ ጎኑ ነው።

ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘ የወልቂጤ ከተማ የተወሰኑ ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ለተከታታይ ቀናት ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ መደበኛ ልምምዳቸውን ሳያከናውኑ መቅረታቸው የተሰማ ሲሆን ነበገው ጨዋታም አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ይገመታል። በተጨማሪ አቡበከር ሳኒ አሁንም ጉዳት ላይ ሲሆን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ተቀይሮ የገባው ዮናስ በርታ እና ሀብታሙ ሸዋለም በማገገም ላይ እንዳሉ ሰምተናል። በአርባምንጭ ከተማ በኩል አሸናፊ ፊዳ በቅጣት አብነት ተሾመ እና ፀጋዬ አበራ ደግሞ በጉዳት ምክንያት አዞዎቹን አያገለግሉም።

ሁለቱ ክለቦች በዋናው ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገኙበትን የነገውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይመሩታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
(ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ልምምድ ያልሰሩ ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ የመኖር አለመኖራቸው ጉዳይ አልታወቀም)

ስልቪያን ግቦሆ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሤ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

ዮናስ በርታ

ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር

አብዱልከሪም ወርቁ

ጌታነህ ከበደ – እስራኤል እሸቱ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – ማሪቲን ኦኮሮ – ተካልኝ ደጀኔ

ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – አሸናፊ ተገኝ

በላይ ገዛኸኝ – ኤሪክ ካፓይቶ