ጅማ አባጅፋር የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ደብዳቤ ፅፏል

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር በወቅታዊ የክለቡ ውጤት ዙሪያ ለአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ደብዳቤ ፅፏል።

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ጅማ አባጅፋር የሊጉን ዋንጫ ከፍ ካደረገ በኋላ ወረድ ያሉ ውጤቶችን ከዓመት ዓመት እያስመዘገበ ይገኛል። በዘንድሮ የውድድር ዓመትም ስድስት ጨዋታዎችን አድርጎ አንዱንም ሳያሸንፍ በዘጠኝ የግብ ዕዳ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በቅርቡ የሥራ-አስኪያጅ እና የቡድን መሪ ለውጥ ያደረገው ክለቡም ከትናንቱ የባህር ዳር ሽንፈት በኋላ ረዘም ያለ ስብሰባ ከተጫዋቾች እና ከአሠልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ካደረገ በኋላ ከሰዓታት በፊት ለአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መፃፉን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

ለክለቡ ዋና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ ለምክትሎቹ ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) እና የሱፍ ዓሊ፣ ለግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ መሐመድ ጀማል እንዲሁም ለክለቡ ወጌሻ ሰናይ ይልማ በተናጠል በተፃፈው ደብዳቤ ላይ ግለሰቦቹ በየድርሻቸው የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።