​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከሀገር ውጭ ያደርጋል

ከስምንት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ከሀገር ውጭ እንደሚያደርግ ታውቋል።

በካሜሮን አስተናጋጅነት ከጥር 1 እስከ 29 ድረስ የሚካሄደው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በሀገር ውስጥ ከማድረግ ይልቅ ከኢትዮጵያ ውጭ ለማድረግ መታሰቡን ሰምተናል።

ከታህሳስ አስራ ስድስት ጀምሮ ሪፖርት እንዲያደርጉ ለተጫዋቾቹ ጥሪ ከተደረገ በኋላ ውድድሩ ከሚያደርግበት ሀገር አቅራቢያ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ተረድተናል። በምዕራፍ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት በአንዱ ሀገር ብሔራዊ ቡድኑ እንደሚጓዝ ብናቅም ያልተጠናቀቁ ነገሮች በመኖራቸው እና በተለያዮ ምክንያቶች ሀገር ሊቀያየር የሚችልበት ዕድል በመኖሩ የሀገሩን ስም ከመግለፅ ለጊዜው ተቆጥበናል። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚሆነው ዝግጅት ባሻገር ከሁለት ሀገራት ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በዛው ለማድረግ እንደታሰበ እና አብዛኛው ነገር መጠናቀቁን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ሀ ከካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶ እና ኬቨርዲ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።