የምንተስኖት አዳነ እና የአዳማ ከተማ ጉዳይ ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ አምርቷል

በአዳማ ከተማ እና በምንተስኖት አዳነ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ማምራቱ ታውቋል።

ከአስር ዓመት በላይ በፈረሰኞቹ ቤት ስኬታማ ቆይታ ያደረገው ምንተስኖት አዳነ ለዘንድሮ የውድድር ዓመት ወደ አዳማ ከተማ ማምራቱ ይታወቃል። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታ  ያደረገው ምንተስኖት ሊጉ ከእረፍት ከተመለሰ በኋላ ግን በቡድኑ ዝርዝር ውስጥ አይገኝም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባደረግነው ማጣራት ተጫዋች ምንተስኖት አዳነ በቅድመ ስምምነት ወቅት ቅድመ ክፍያ በመስማማት ቼክ እንደተቀበለ እና ክፍያው ሊፈለም ባለመቻሉ እንዲሁም የጥቅምት ወር ደሞዝ አለመከፈሉን ተከትሎ ለክለቡ የአቤቱታ ደብዳቤ ሲያስገባ ክለቡ በአንፃሩ ምንተስኖትን ለአንድ ዓመት ማገዱን እና የወሰደውን ቼክ ተመላሽ እንዲያደርግ በደብዳቤ አሳውቀዋል።

በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልሆነው ምንተስኖት ”ባልተከፈለኝ ደሞዝ ላይ ይባስ ብሎ ክለቡ አግዶኛል” ሲል ያለውን መረጃ በማጠናከር ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ቅሬታውን በደብዳቤ ገልፆ በኋላ ያለፉትን አስራ አምስት ቀናት ቡድኑን ሳይቀላቀል ቆይቷል። የቼኩም ሒደት በጠበቃው አማካኝነት ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ ሲገለፅ ጉዳዩን የያዘው የዲሲፕሊን ኮሚቴም በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ ሌሎች አምስት የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች በቅድመ ስምምነት መሠረት ክፍያው ያልተፈፀመላቸው በመሆኑ ቅሬታ እያሰሙ እንደሆነ ሰምተናል።