የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-2 ሀዲያ ሆሳዕና

ሀድያ ሆሳዕና የውድድር ዓመቱን ድል መከላከያን ከረታ በኃላ አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

የተጫዋቾቹ ጥረት

ዛሬ ከምንግዜውም በላይ ከነበርንበት ቦታ ትንሽ ገፋ ለማለት ነበር፤ እርሱም ተሳክቶልናል። ግን አጨዋወታችን እንደምንገጥማቸው ቡድኖች ይቀያየራል። እኛ የለመድነው ጨዋታ ተጫውቶ ለመሄድ ነው። ከሞላጎደል ዛሬ እንደበፊቱ ባይሆንም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።

የአማካይ ቁጥር ስለማብዛት

አሁን ባለንበት ሁኔታ መሐል ሜዳ ላይ መጫወት አስቸጋሪ ነው። በመስመር በኩል ለመጠቀም ፊት ላይ ለማጥቃት የቁጥር ማነስ ነበረው እና ከመስመር እየሄዱ መሀል ላይ ተደርበው እንዲጫወቱ ሰሞኑን የነበረብን ችግር ጎል ማስቆጠር ስለነበር ለዛ ነው መሐሉን ያበዛነው እንጂ ለመከላከያ ብቻ አይደለም። አንደየጨዋታዎቹ የሚቀያየሩ ናቸው።

የዚህ ድል ትርጉም

በእርግጥ ማንም ሰው ሲሰራ ነጥብ ይፈልጋል። እኔም ቡድኑ አዲስ እንደመሆኑ ሊጉ ካለው ጥንካሬ አንፃር አሁን ካለንበት ለመሸሽ ሙሉ ሦስት ነጥብ ያስፈልገናል። አሁን ከሽንፈት ወደ ማሸነፍ እየመጣን ነው። አሁን ከእኔ ይልቅ የቡድኑ እድገት የሚያስደስተኝ የዛሬው ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ ውጤት እንዲኖረው ነው የምፈልገው። ስታሸንፍ ደስ ይልሀል በራስ መተማመንህም እየጨመረ ይሄዳል። ነጥብ ስትጥል ትወርዳለህ እስታሸንፍ ግን ለቀጣዮ ጨዋታዎች ይጠቅማል።

የዑመድ አለመኖር እና ስለ አሸናፊ ቡድን ቀጣይነት

ዛሬ ላይ እንዲህ ብሎ መወሰን አይቻልም። የአንድ ሳምንት ጊዜ ስላለ በልምምድ የምናያቸው ነገሮች አሉ። አሸናፊ ቡድን ውስጥ ሁሉም ትክክል ነው ማለት አይቻልም። ሁሉም መጥፎ ነው ማለት አይቻልም። ኡመድ የተጎዳብን ልምምድ ላይ ነው ስለዚህ ዛሬ ላይ ሆኜ የምወስነው ነገር የለም።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ

የቡድኑ እንቅስቃሴ

የጨዋታችን መንገድ ጥሩ ነበር ። የመጀመርያው ጎል ሲቆጠር ተጫዋች ተጎድቶብን ነበር። በእኔ እምነት ዳኛው ጨዋታውን ከቁጥጥር ውጭ አድርጎታል። ብዙ ድራማ የበዛበት ነበር። ብዙ መተኛት ማንቀላፋት ነበረበት። ከዛ ውጭ ማድረግ የሚገባውን ሀድያ አድርጎ ወጥቷል። በእኔ ግምት ለዳኛው ከብዶታል።

ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ያሰቡት ስለመሳካቱ

እኛ የተጫወትነው አራት አምስት አንድ ነው። ያቺ ጎል ከተቆጠረችብን በኋላ ያለ መግባባት ተፈጥሮ ነበር። መጀመርያ የተጎዳ ተጫዋች ነበር፤ ቢወጣ ጥሩ ነበር። ከዛ ውጭ ማሸነፍ መሸነፍ እንዳለ ሆኖ ማድረግ የሚገባንን አድርገናል።

በጨዋታው ላይ የተወሰደው ብልጫ የቱ ነው ?

የመጀመርያው ጎል ነች፤ ተጫዋቻችን ተጎድቶ ወደ መከላከል ባለመሄዱ ለእነርሱ ማግባት መነቃቃት ፈጥሯል። ምክንያቱም ባልጠበቁት ሁኔታ ነው ጎል የተቆጠርው። ያ ተጫዋች እግሩን ባይጎዳ መሸፈን ቢችል ኖሮ ጎል አይቆጠርም ነበር። በዛች አጋጣሚ በተፈጠረች ጎል ሊያሸንፉ ችለዋል።

ዛሬ የቀጥተኛ አጨዋወት ድክመት

ደካማነት ሳይሆን ጥሩ መከላከል አድርገዋል እነርሱ። ብዙ ኳሶች ወደፊት በመሄድ ሙከራ አድርገናል። ጠንካራ እና ጉልበት የተቀላቀለበት መከላከል የሚሰራ ቡድን ስለሆነ በዛ ደረጃ ተከላክለዋል ብዬ አስባለው።