ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር በተመለከትንበት እና አዳማ ከተማዎች በርከት ያሉ የግብ እድሎችን ፈጥረው ወደ ግብነት መለወጥ ባልቻሉበት ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳን ሲረቱ የተጠቀሙበትን የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች በሙሉ በዛሬው ጨዋታ የተጠቀሙ ሲሆን በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከሲዳማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በታደለ መንገሻ ምትክ ደስታ ዮሀንስን ብቻ ተክተው የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ 20 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች በመሀከለኛው የሜዳ ክፍል ከሚነጣጠቋቸው ኳሶች በዘለለ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተቀናጀ መልኩ ጥቃቶችን መሰንዘር ያልቻሉበት ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተመለከትነው የመጀመሪያ ሙከራም በ12ኛው ደቂቃ ከምኞት ደበበ እግር የነጠቀውን ኳስ አሜ መሀመድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ቻርልስ ሉክዋጉ ያዳነበት ኳስ ነበር።

ቀስ በቀስ የጨዋታ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ወደ ራሳቸው ሜዳ እንዲገፉ ማድረግ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ኳሱን በማንሸራሸር ክፍተቶች ለማግኘት ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል።

በጨዋታው ከወትሮው በተለየ በርከት ያሉ ስህተቶች ሲሰራ የነበረው ምኞት ደበበ በ28ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተመታን ኳስ ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት ሳጥን ጠርዝ ላይ የሰራውን ስህተት ተከትሎ አብዲሳ ጀማል አደገኛ ቦታ ላይ ያገኘውን ጥሩ እድል መጠቀም ሳይችል የቀረ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃም እንዲሁ በጥሩ የቅብብል ሂደት የመጣውን ኳስ ሚሊዮን ሰለሞን ከቀኝ መስመር አክርሮ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ አቡበከር ወንድሙ መጠቀም ሳይችል ቀረ እንጂ አዳማ ከተማዎች ጫናቸው አየል ብሎ ተመልክተን ነበር።

በአጋማሹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ34ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሀንስ ከግራ መስመር ወደ ግብ የላከው እና ጀማል ጣሰው በቀላሉ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራቸው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ፍላጎት ጨዋታውን የጀመሩት ጊዮርጊሶች በ52ኛው ደቂቃ የአብስራ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር የተነሳውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ከተቆጣጠረ በኃላ ወደ ግብ የላከውን እና ጀማል ጣሰው ባዳነበት ኳስ ነበር የጀመሩት።

ነገርግን አዳማ ከተማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን በመቀጠል በ55ኛው እና በ57ኛው ደቂቃ ላይ በአሜ መሀመድ አማካኝነት ሁለት አስደናቂ የግብ አጋጣሚዎችን ያመከኑ ሲሆን በተመሳሳይ በ59ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው ከግቡ ትይዩ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ አዳማዎች የጨዋታውን መሪነት ለመውሰድ በጣሙን የቀረቡባቸው ሶስት አጋጣሚዎች ነበሩ።

በ74ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን አጋጣሚ ከቀኝ መስመር መነሻውን ሲያደርግ ኦሮ-አጎሮ ሳጥን ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብ ቢልክም ጀማል ጣሰው በግሩም ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ እየደረሱ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ውጤቱን መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል በተለይም አማኑኤል ጎበና ፣ አብዲሳ ጀማል እና ደስታ ዮሀንስ ያመከኗቸው ኳሶች አስቆጭ ነበሩ።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ11 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ8 ነጥብ ዘጠኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።