የአሠልጣኞች አስተያየት | አርባምንጭ ከተማ 0-0 ጅማ አባጅፋር

ያለ ግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ጋር ቆይታ አድርጓል።

መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረናል። ተለዋዋጭ አቀራረብ ለመጠቀምም ሞክረናል። የተሻሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችንም ለመፍጠር ሞክረናል። ግን እንዳሰብነው አልተሳካም። ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። የመጣውን ተቀብሎ ለቀጣይ መስራት ነው የሚያዋጣው።

በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረገለቸው ለውጦች?

በሁለት መልኩ ነው ለውጡ። ከግለሰብም ሆነ ከታክቲክ አንፃር ነው ለውጦቹ የነበሩት። በተወሰነ መልኩ በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ነገር አይቻለሁ።

በጨዋታው ብዙ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች እምብዛም ስለመሆናቸው?

ጅማ የግብ ክልል ከደረስን በኋላ በራስ አተገባበር ነው የሚወሰነው። እነሱም ለመከላከል ፍላጎት አሳይተው ነበር። እኛም ግን በምንፈልገው መንገድ አልሄድንም።

እስከ ዘጠነኛ ሳምንት ምን ደረጃ ላይ ቡድኑ ይቀመጣል?

አሁን ካለን የተሻለ ደረጃ ይዘን እንጨርሳለን። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች ጥሩ ነገር አለን። ከእረፍት መልስም እስካሁን አልተሸነፍንም። ግን አለመሸነፍ በቂ አይደለም። ተደጋጋሚ ማሸነፎች ያስፈልጉናል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ስለመሆኑ?

እንዳልከው ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነበር። ተጫዋቾቼ ባለማሸነፋቸው የመጣ ጫና አለ። ከዛ አኳያ ያገኘናቸውን በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን መጠቀም አልቻልንም። ዞሮ ዞሮ የመጀመርያ ነጥባችንን አግኝተናል።

ስለ እረፍት ሰዓት ቅያሪ?

የምፈልገውን ታክቲክ ስላልተገበረልኝ ነው ቅያሪ ያደረግኩት።

ውጤቱ ለቀጣይ መነሻ ስለመሆኑ ?

ከዜሮ አንድ ይሻላል፤ ስለዚህ መነሻ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።

ስለ እረፍት ሰዓት ምክክራቸው?

ተጫዋቾቼ ተረጋግተው እንዲጫወቱ ነው የመከርኳቸው። ውጥረት ያለበት ውድድር ነው። ይህንንም ውድድር ቀልባቸውን ሰብስበው ካልተጫወቱ ማሸነፍ አይቻልም። አለመረጋጋት እና መቸኮል አለ። እነዚህን ቀርፈው ተረጋግተው እንዲጫወቱ ነው የመከርኳቸው።

እስከ ዘጠነኛው ሳምንት ከግርጌው ስለመላቀቃቸው?

እግርኳስ ነው ምን እንደሚከሰት አይታወቅም።