የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 0-2 ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ተከታታይ ድል ድሬዳዋ ላይ ካስመዘገበ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን ብለዋል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

“ጥሩ ነው፤ የቀደሙ ጨዋታዎቻቸውን ተመልክተን ይበልጥ ነፃ ሆነው ይጫወታሉ ብለን አስበን ነበር። ነገርግን ያ አልሆነም። ይበልጥ ወደ ግባቸው ቀርበው ነው ይጫወቱ የነበሩት። ከባለፈው ጨዋታ ያሻሻልነው ብዬ የማስበው ነገር ግብ ካስቆጠርን በኋላ ጨዋታውን በተሻለ ለመቆጣጠር ችለናል።”

ከ35ኛው ደቂቃ በኃላ ድሬዳዋ የተሻለ ስለመሆኑ

“ካለፉት ጨዋታዎች ተነስተን መናገር የሚቻለው ቡድኖች ግብ ሲቆጠርባቸው ሆነ ብልጫ ሲወሰድባቸው በተወሰነ መልኩ የነበራቸውን ነገር እየለቀቁ ይመጣሉ። ስለዚህ መጀመሪያ እንደነበሩት አይሆኑም። በሌላ አይነት አመጣጥ ስለሚመጡ የእኛ ልጆች ለእሱ መልስ መስጠት አለባቸው። ይህን ክፍተት የሚፈጥረው ተጫዋቾች ከመጀመሪያው ነገር ወጥተው ራሳቸውን እስኪያስተካክሉ ብልጫ ሊወሰድብህ ይችላል።”

ስለ ፍፁም ቅጣት ምቶቹ

“ለእኛ ስለሆነ ሳይሆን ሳጥን ውስጥ የትኛውም ንኪኪ እንደውም አቡበከር ወደ ጎል እየሄደ ነው ለጎል ጀርባህን ሰጥተህ እንኳን ንኪኪዎች ካለ ፍፁም ቅጣት ምት ነው ፤ የመጨረሻው ውሳኔ ግን የዳኞች ነው።”

ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጥሩ ነበር በተለይ እነሱ ኳስ መስርተው ስለሚጫወቱ ጫና ፈጥረን እነሱ በሚሳሳቷቸው ኳሶች ለማስቆጠር ነበር እስከ 70ኛው ደቂቃ በምንፈልገው መንገድ ሄዶልን ነበር ከዛ በኃላ በሰራናቸው ስህተቶች ግቦች ተቆጥረውብናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ስለመሆናቸው

“የእነሱ የኳስ ቁጥጥር በራሳቸው ሜዳ የሚነካኩ እንደመሆናቸው ብዙም ለእኛ ችግር አልነበረውም ዋናው ወደ እኛ ሜዳ ይዘው እንዳይገቡ ማድረግ ነበር የፈለግነው ከዛም በመልሶ ማጥቃት ወደ እነሱ ለመሄድ ነበር ያሰብነው ይህ ተሳክቶልን ነበር ነገርግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተበላሽቶብናል።”

ስለ ሁለቱ ፍፁም ቅጣት ምቶች

“ስድስት ነጥብ ያጣነው በዳኞች ስህተት ነው ፤ በይበልጥ የመጀመሪያው አስመስሎ ነው የወደቀው 150% ፍፁም ቅጣት ምት አልነበረም። ቢጫ ካርድ እና ለእኛ ቅጣት ምት ነበር የሚገባን። የጨዋታውን መንፈስ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ አጋጣሚ ነበር።”