ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው የፅሁፋችን ክፍል አካል ናቸው።

👉 ኦኪኪ አፎላቢ እና የሲዳማ ደጋፊዎች

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሲዳማ ቡና መለያ ቡድኑ ላለመውረድ ባደረገው ጥረት ሰባት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ሚናን የተወጣው ኦኪኪ አፎላቢ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ መለያ የቀድሞ ቡድኑ ላይ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን 4-0 በረታበት ጨዋታ በፋሲል ከነማ መለያ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሱዳኑ አል ሂላል ላይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ግቡን በቀድሞው ክለቡ ላይ ማስቆጠር በቻለበት ጨዋታ የቀድሞ ክለቡ ደጋፊዎች የተለየ ፍቅርን አሳይተውታል።

በክለባቸው ሁኔታ ደስተኛ ያልነበሩት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በተደጋጋሚ የኦኪኪን ስም እየጠሩ ሲያሞካሹት ተደምጧል። እሱም በአፀፋው ግቡን ካስቆጠረ በኃላ ደስታውን ያልገለፀ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽ እንደተጠናቀቀም ለሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ያለውን ፍቅር እና አክብሮት አሳይቷል።

👉 ጥቁር እና ነጩ የዓለምብርሃን ይግዛው የጨዋታ ቀን . . .

በ2011 ወደ ፋሲል ከነማን ዋና ቡድን የማደግ ዕድል ያገኘው ወጣቱ ዓለምብርሀን እንደሰሞኑ ጨዋታዎች ጎልቶ የወጣበት ጊዜ አለ ማለት አይቻልም። በመስመር አጥቂነት እና አማካይነት አልፎ አልፎ ተቀይሮ በመግባት ሲጫወት የምናውቀው ዓለምብርሀን ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ አጋማሽ ተቀይሮ ከገባ ወዲህ በወጥነት በአሰላለፍ ውስጥ እየተመለከትነው እንገኛለን።

አብዱልከሪም መሀመድ እና ሰዒድ ሁሴን ባሉበት የቀኝ መስመር ተከላካይነት ቦታ ላይ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ታምኖበት ከመሰለፍ ባሻገር በየጨዋታዎቹ ላይ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ ጎልቶ መውጣት የቻለ ሲሆን በሰባተኛው ሳምንት ደግሞ ሲዳማ ቡና ላይ ግብ እስከማስቆጠር ደርሷል።

ተጫዋቹ የእግርኳስ ህይወቱን የሚያቀናበትን አጋጣሚ በአግባቡ እየተጠቀመ ቢታይም በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ላይ ያሳየው ባህሪ ግን ወደ ኋላ እንዳይጎትተው ያሰጋል። የፋሲል ከነማው የመስመር ተጫዋች ድንቅ የጨዋታ ቀን ቢያሳልፍም በአንድ ቅፅበት የሲዳማ ቡናው መሐሪ መናን አንገት ያነቀበት ድርጊት መነጋገርያ ነበር። አሰልጣኝ ስዩም ከበደም ይህንን የተጫዋቹን ተግባር ዕረፍት ሰዓት ላይ ሲገስፁ ታይተዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይም ተጫዋቹ በዳንኤል ዘመዴ ተቀይሮ ወጥቷል።

መሰል ስሜታዊነቶች እና እነሱን ተከትለው የሚመጡ ቅጣቶች ተጫዋቾች ያገኙትን የመሰለፍ ዕድል እንዲያጡ ሊያደርጉ መቻላቸው ሲታሰብም ዓለምብርሀን ከሀዲዱ እንዳይወጣ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ያሳየ ሆኗል።

👉 ባለሁለት ሳንባው ኢያሱ ታምሩ

ሀዲያ ሆሳዕና የመጀመሪያ ድሉን ባሳካበት ጨዋታ ምንም እንኳን ግቦቹን ያስቆጠረው ሀብታሙ ታደሰ የትኩረቶች ማዕከል ቢሆንም የእያሱ ታምሩ አበርክቶ በቀላል የሚታይ አይደለም።

በመስመር ተመላሽነት የተሰለፈው እያሱ ታምሩ ሀብታሙ ላስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ኳሶቹን አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ሙሉ መስመሩን እየዘጋ ይጫወት የነበረበት መንገድ እጅግ የተለየ ነበር።

በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ቡድኑ የሚጠብቅበተን የሰጠው እያሱ ይህን ለዘጠና ደቂቃ ያለመዋዠቅ በላቀ ትጋት ሲያደርግ መመልከታችን ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ በቋሚነት የመሰለፍ ዕድልን ፍለጋ ሆሳዕና የደረሰው ተጫዋቹ አስገራሚ የሜዳ ማካለል አቅሙንም ሆነ ታጋይነቱን በሆሳዕና ቤት በሚገባ ዳግም እያስመሰከረ ይገኛል።

👉 ባለሁለት ግቦቹ 

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው ለቡድናቸው ሁለት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ባህርዳር ከተማ ወላይታ ድቻን 3-1 በረቱበት ጨዋታ ፍፁም ዓለሙ ቡድኑን ባለድል ያደረጉ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህም ከዚህ ቀደም በአርባምንጭ ከተማ ሲሸነፉ እና ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ካስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ጋር ተዳምሮ በሊጉ ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ አራት ከፍ ማድረግ ችሏል።

የአምና በ29 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው አቡበከር ናስር ዘንድሮ እንደአምናው ሁሉ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር ቢቸገርም በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ባስቆጠራቸው ሁለት ሁለት ግቦች በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ በአራት ግቦች ደረጃውን ከአምስት ተጫዋቾች ጋር ተጋርቷል።

ጎል እንደሰማይ ርቆት የከረመው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ መከላከያን በመርታት የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል። ታድያ ይህን ድል ሲያስመዘገብ አጥቂው ሀብታሙ ታደሰ ሁለት ግቦችን ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን ከጎል እና ከሦስት ነጥብ አስታርቋል።

👉 በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ይታትር የነበረው ይገዙ ቦጋለ

ሲዳማ ቡናዎች በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በቁጥር በርከት ባሉ ደጋፊዎቻቸው ፊት አስደንጋጩን ሽንፈት ሲጎነጩ በሲዳማ ቡናዎች በኩል ብቸኛው ተስፋ ሰጪ ነገር የይገዙ ቦጋለ ያለመታከት ያደርግ የነበረው የሜዳ ላይ ጥረት ብቻ ነበር።

በአራት ግቦቹ በጣምራ የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ይገዙ ቦጋለ እጅግ አስከፊ እንቅስቃሴን ባደረገው ቡድኑ ውስጥ በግሉ አቅሙ የፈቀደውን ለማድረግ ጥረት አድርጓል። ሙሉ ዘጠና ደቂቃን የተጫወተው ይገዙ በጥልቀት ወደ ኋላ በመሳብ እንቅስቃሴዎች ወደ ማጥቂያው ሲሶ እንዲደርሱ ለማድረግ እንዲሁም በግሉ ተጫዋቾችን በማለፍ የተሻለ ነገር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረትን ሲያደርግ ተስተውሏል።

እርግጥ ጥረቱ በጎሎች ባይታጀብም በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰኑ የጨዋታ ደቂቃዎች ለነበራቸው አንፃራዊ መነቃቃት የይገዙ ቦጋለ ሚና ቁልፍ ነበር። ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ በነበሩ ጨዋታዎች የደጋፊዎችን ልብ መሉ ለሙሉ ማግኘት ላልቻለው ተጫዋቹ እንደ ቡድን ደካማ በነበሩበት የጨዋታ ዕለት ያሳየው አስደናቂ ታታሪነት በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የተሰጠው እና አድናቆት ያስገኘለት ነበር።

👉 ጥሩ ቀን ያላሳለፈው ምኞት ደበበ

ሀዋሳ ከተማን ለቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ ወዲህ በፍጥነት የተላመደ ይመስል የነበረው ምኞት ደበበ ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋተ በስህተት የተሞላ የጨዋታ ቀን አሰልፏል።

የአስቻለው ታመነን ወደ ፋሲል ከነማ ማምራቱን ተከትሎ በቦታው የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ብርቱካናማ በቀዮቹ ቤት የደረሰው ምኞት ደበበ በመጀመሪያዎቹ ስድስት የጨዋታ ሳምንት የነበረው እንቅስቃሴ በክለቡ ለረጅም ጊዜ የቆየ እንጂ በክረምቱ የተቀላቀለ ተጫዋች አይመስልም ነበር።

ነገር ግን ከቀድሞዉ ክለቡ አዳማ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ምኞት ባልተጠበቀ መልኩ ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲፈፅም ተመልክተናል።

👉 የጀማል ጣሰው ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን

በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ እየተጫወተ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ አባል የሆነው ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በአንዳንድ ጨዋታ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን መነሻነት ስህተቶችን ሲፈፅም ይስተዋላል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ በተለይ በሁለት አጋጣሚዎች የተጫዋቹን ከልክ ያለፈ የራስ መተማመን የተመለከተንበት ነበር።

በጀመሪያው አጋማሽ በአንድ አጋጣሚ ወደ ውጪ የሚወጣ ኳስን በአላስፈላጊ ሁኔታ በደረት አበርዳለው ብሎ ደረቱ ላይ ለማሳረፍ ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከምንም የማዕዘን ምት እንዲያገኙ አስችሏል።

በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በረጅም ያሻገሩትን ኳስ ተከትሎ ግብ ክልሉን ለቆ ወጥቶ በአደገኛ ሁኔታ በተረከዝ ለቡድን አጋሩ ደስታ ዮሐንስ አቀብላለሁ ብሎ ጋቶች ለጥቂት መቆጣጠር ሳይችል ቀረ እንጂ ቡድኑን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል አጋጣሚ ነበር።

እርግጥ ዘመናዊው እግርኳስ ግብ ጠባቂዎች በተወሰነ መልኩ ኃላፊነት ወስደው እንዲጫወቱ የሚያስገድድ እንደሆነ ቢታመንም ይህን ኃላፊነት መውሰድን ያለ ልክ ለመጠቀም ጥረት ማድረጉ ቡድንን ለአደጋ የማጋለጥ ዕድሉ ስለሚጨምር ጥንቃቄ ሊደረግበት የግድ ይላል።

👉 ተስፋ የሚሰጠው የአሜ መሀመድ እንቅስቃሴ

ወጣቱ አጥቂ ከጅማ አባ ጅፋር ቆይታው በኋላ ወደ ፊት ለመጓዝ የተቸገረውን የእግር ኳስ ህይወቱን ዳግም ወደ መስመር ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

አምና በወልቂጤ ከተማ ወጣ ገባ ያለን ጊዜ ያሳለፈው አሜ ዘንድሮም በአዳማ ከተማ ቤት የቀደመ አስደናቂ የግብ ማስቆጠር አቅሙን ለማግኘት እየጣረ እንደሚገኝ እየተመለከተን እንገኛለን። በተለይም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ጥረቱ በግብ አይታጀብ እንጂ መልካም የሚባል እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል።

ከግራ መስመር መነሻውን ያደረገው አሜ መሀመድ በመስመርም ሆነ ወደ ወደ መሀል እያጠበበ በመግባት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ሲፈተን ተመልክተናል። በጨዋታው አዳማዎች ከፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ውስጥ በአብዛኛዎቹ ላይ አስደናቂ አፈትላኪ ሩጫዎችን በማድረግ ዓይነተኛ ድርሻን ተወጥቷል።

በተጨማሪም ቡድኑ ከኳስ ውጪ በሚሆንባቸው አጋጣሚዎችም ወደ ኋላ እየተመለሰ የመስመር ተከላካዮቹን ለማገዝ ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነበር።

👉 እየተሻሻለ የሚገኘው የአብስራ ሙሉጌታ

ከቅዱስ ጊዮርጊስ የዕድሜ እርከን ቡድን የተገኘው ወጣቱ የአብስራ ሙሉጌታ የጨዋታ ደቂቃን ፍለጋ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ያመራበት ውሳኔ ትክክለኛ ስለመሆኑ እየታየ ይገኛል።
በአዲሱ ክለቡ በወጥነት በመሀል ተከላካይነት እየተጫወተ የሚገኘው የአብስራ በጅማ አባ ጅፋር የመሀል ተከላካይ ስፍራ አጣማሪዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ ቢለያዩም በግሉ ግን ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል።

ከኳስ ጋር ጥሩ ክህሎት ያለው ተጫዋቹ በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው ጥንካሬ እና የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ተገንዝቦ ለመቋረጥ ያለው ዝግጁነት ከዕድሜ ዕኩዮቹ የተለየ ያደርገዋል። እርግጥ በሊጉ ደካማው የተከላካይ መስመር ባለቤት ከሆነው ስብስብ ውስጥ ጥሩ ስለሆነ የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ማውራት ከባድ ቢመስልም የአብስራ ሙሉጌታ እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴ ግን በልዩነት መታየት የሚፈልግ ነው።

👉 የሀዋሳ ከተማ አጥቂ መስመር

ሦስት ፈጣን የሆኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ያሉት ሀዋሳ ከተማ ከብሩክ በየነ ፣ መስፍን ታፈሰ እና ኤፍሬም አሻሞ ባለፉት ጨዋታዎች በቂ ግልጋሎት አግኝቷል ብሎ መውሰድ አይቻልም።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ሦስቱም አጥቂዎች ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ሦስት ግቦችን ለቡድናቸው ማስቆጠር ችለዋል።

በመሰረታዊነት የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ እነዚህን ሦስት አጥቂዎችን ከተጋጣሚ የተከለካይ መስመር ጀርባ እንዲሮጡ በማድረግ ላይ ያተኮረ ቢመስልም ሀዋሳ ከተማዎች በተለይም ሰበታ ከተማ በመጨረሻው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የታየበትን በመስመሮች በኩል የሚሰነዘርን ጥቃት የመመከት ድክመት በሚገባ ለመጠቀም ጥረቶችን አድርገዋል።

በዚህም እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ የሰበታ ከተማ ተከላካዮችን ከመፈተን ባለፈ በመስመር በኩል የቁጥር ብልጫን በመውሰድ ኳሶችን ወደ ሳጥን ለማድረስ ያደረጉት ጥረት ግቦችንም ያስገኘላቸው ነበር። በተጨማሪም በሚፈለገው ልክ ግብ እያስቆጠሩ ያልነበሩት ሦስቱ አጥቂዎች አንድ ላይ ወደ ግብ አግቢነት የመመለሳቸው ጉዳይ ለቡድኑ ትልቅ እፎይታን የፈጠረ ነው።