ሪፖርት | በመጨረሻም ሰበታ ከተማ አሸንፏል

በስምንተኛ የጨዋታ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች በክሪዚስቶም ንታምቢ ብቸኛ የግንባር ኳስ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል ማሳካት ችለዋል።

ጅማ አባጅፋሮች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለግብ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም አልሳሪ አልመህዲ እና ሮጀር ማላ ወጥተው በምትካቸው ሚኪያስ ግርማ እና እዮብ ዓለማየሁን የተኩ ሲሆን በተቃራኒው ሰበታ ከተማ በሀዋሳ ከተረታው ስብስብ ውስጥ ስድስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ለዓለም ብርሃኑ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ፍፁም ተፈሪ ፣ ክሪዚስቶም ንታምቢ እና ፍፁም ገብረማርያም በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ከሚገኙበት የወራጅ ቀጠና ለመላቀቅ የተሻለ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ በተጠበቀው እና በከፍተኛ ንፋስ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የሰበታ ከተማ ቀጥተኛ አጨዋወት አደገኛ የነበረበት ነበር ፤ በአጋማሹ ሰበታዎች መሀል ሜዳ ላይ የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፍጥነት ከጅማ አባጅፋር ተከላካዮች በስተጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል።

በ3ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ስፍራ በረጅሙ የላኩለትን ኳስ ተጠቅሞ ዱሬሳ ሹቢሳ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከመስመር ሰብሮ ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ሰበታዎች በ13ኛው ደቂቃ ሃይለሚካኤል ከግራ መስመር እንዲሁም በ27ኛው ደግሞ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ ያሻገሩለትን ኳስ ፍፁም ሳጥን ውስጥ ሆኖ ቢያገኛቸውም ወደ ግብ የላካቸውን ኳሶች አላዛር ሲያድንበት በተመሳሳይ በ17ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ የመታውን ኳስ እንዲሁ አላዛር ማርቆስ ሊያድንባቸው ችሏል።

ጨዋታው 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በስታዲየሙ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት ሁለት ፖውዛዎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ለ13 ያክል ደቂቃዎች ተቋረጦ በቀጠለው ጨዋታ ሰበታዎች የበላይነታቸውን በግብ ማጀብ ተሳናቸው እንጂ የበላይነታቸውን አስቀጥለዋል።

በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል ያሰቡ የሚመስሉት ጅማዎች በአጋማሹ በመከላከሉ የነበራቸው አደረጃጀት ደካማ የሚባል ነበር በማጥቃቱም መስዑድ መሀመድ በግሉ በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጭ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመከላከሉ ደስተኛ ያልነበሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በላይ አባይነህን አስወጥተው በምትኩ ምስጋናው መላኩን በማስገባት የሰበታን አጥቂዎች ፍጥነት መቋቋም ተስኖት የነበረውን የቡድኑ የኃላ ሶስት ተከላካይ ላይ ሽግሽጎችን አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተሻሻለ መነቃቃት የተጀመረ ቢመስልም በሂደት ግን ጨዋታው እንደ መጀመሪያው ሁሉ መቀዛቀዞች ታይተውበታል።

የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ጅማ አባጅፋሮች ነበሩ በ47ኛው ደቂቃ ለማጥቃት ሙሉ በሙሉ ነቅለው የወጡትን የሰበታ ተጫዋቾች የተውትን ክፍት ሜዳ ተጠቅመው ጅማዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን አጋጣሚ ዱላ ሙላቱ ባለመረጋጋት ባመከናት ፍፁም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ነበር።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ለማስመዝገብ የማጥቃት ፍላጎቶች ቢኖሩም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የነበረው የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን ጥድፊያ የተሞላበት በመሆኑ ፍሬያማ ለመሆን ተቸግረው ተስውሏል።

ነገርግን በ79ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማ ያገኙትን የማዕዘን ምት ሳሙኤል ሳሊሶ በግሩም ሁኔታ ያሻማውን ኳስ ክሪዚስቶም ንታንቢ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ በግንባሩ በመግጨት ሰበታን መሪ ያደረገችን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በቀሩት ደቂቃዎች ጅማ አባጅፋሮች በሙሉ ሀይላቸው ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ በተቃራኒው ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በፍፁም መከላከል መሪነታቸውን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል።

የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ያስመዘገቡት ሰበታ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ ሰባት በማሳደግ ባሉበት 15ኛ ቦታ ሲረጉ ጅማ አባጅፋሮች በአንድ ነጥብ አሁንም በሊጉ ግርጌ ይገኛሉ።