የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-1 ሰበታ ከተማ

ስምንተኛው የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ባሸነፈበት ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

በርካታ ጎሎችን ስተናል። እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል ፤ ተሸንፈናል።

አሁን ስለሚገኙበት ስሜት

ከሽንፈት ምንም ጥሩ ስሜት አይኖርም። ያለው ውጤት በፍፁም የሚያስደስት አይደለም። ደጋፊውም ይህንን ውጤት አይቀበለውም። ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም።

ስላለባቸው ጫና

ከዚህ በላይ መስራት አልችልም። ባሉት ልጆች የምችለውን ነው የምሰራው። ያለን አቅም እንደሚታየው ነው። መጀመሪያ ላይ የተበላሸብን አመላመል ላይ ነው። ይህንን ቃል ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ተናግሬዋለው። እና መጀመሪያ የተበላሸውን ነገር አሁን ለማስተካከል ይከብዳል።

ከክለቡ ጋር ስለመለያየት

እኔ በድኑን ለማስተካከል እጥራለሁ። የተቻለኝን ያህል እሄዳለሁ ፤ ከዚህ በኋላ የክለቡ ውሳኔ ነው።

 

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራሁ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው

ከጨዋታው ስሜቱ ይቀድማል ፤ ስሜቱ ደስ የሚል ነው። ምክንያቱም ክለባችን ማሸነፍ አልቻለም ነበር። ለማሸነፍ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እና ፍላጎት ነበረን ዛሬ። በርካታ የግብ አጋጣሚዎችንም አግኝተናል ፤ የመጠቀም ድክመታችን እንደተጠበቀ ሆኖ። ስለዚህ ከእንቅስቃሴው በፊት ለእኔ ስሜቱ ነው የሚቀድመው። ወደ ጨዋታው ስንመጣ ጨዋታው ላይ አንድ እና አንድ የማሸነፍ ፍላጎት ነው የነበረን። ተጋጣሚያችን እኛን ማሸነፍ ቢችል በነጥብ እንስተካከላለን። ‘ይሄን ጨዋታ ካላሸነፍን የበለጠ ወደ ከባድ ነገር ውስጥ እንገባለን’ የሚል ስሜት ስለነበር ትኩረት አድርገን የገባነው ማጥቃቱ ላይ ነው። ታክቲካሊ የታሰረ ነገር አልነበረውም። ክፍት ነው ጨዋታው ፤ ጎል ለማግባት ማለት ነው። ከዛ ጎል ካገባን በኋላ በተወሰነ መንገድ የመከላከሉን ኃላፊነት ወስደናል። ጨዋታው በዚህ መንገድ ይገለፃል።