ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በ8ኛ የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች በሁለተኛው ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉 የትኩረት ማዕከል የነበረው ጌታነህ ከበደ

በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከተናቸው ያልተለመዱ ክስተቶች አንዱ የጌታነህ ከበደ አድናቂ ማለያውን ጠይቃ በጨዋታው መጨረሻ ያገኘችበት ሂደት አንዱ ነበር።

በጨዋታው ከታደሙ የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች መካከል አንዲት እንስት “ጌታነህ ጀግናችን ማሊያህን እፈልጋለሁ ማሊያህን ስጠኝ !!” የሚል ፅሁፍ የሰፈረበትን ወረቀት ይዛ በስታዲየሙ መታየቷን ተከትሎ በዲኤስቲቪ እና በሌሎች ፎቶግራፈሮች ትኩረትን ስባ ምስሎቿ በተለያዩ መንገዶች በማህበራዊ ትስስር ገፆች ሲዘዋወር ተመልክተናል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በዲኤስቲቪ ሰዎች አማካይነት እንስቷ ወደ ሜዳ ወርዳ ጌታነህ ከበደ ጨዋታውን ጨርሶ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመራ በጥያቄዋ መሰረት ማለያውን አግኝታለች።

ይህ ነገር በሌላው የዓለም ክፍል የተለመደ ቢሆን እኛ ሀገር ግን እንደ ብርቅ መታየቱ ያስገርማል። ክለቦች በውድድር ዘመኑ እጅግ ውስን በሆኑ መለያዎች መጠቀማቸውን ተከትሎ መሰል ሂደቶች በቀደሙት ጊዜያት የሚታሰቡ ባይመስልም በተለይ ዘንድሮ ክለቦች ይፋዊ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት እየፈፀሙ መምጣታቸውን ተከትሎ ይህ አካሄድ እየተቀየረ እንደመጣ የጌታነህ ከበደ ድርጊት ማሳያ ነው። ክስተቱ በስፖርቱ አፍቃሪ ዘንድ ያገኘው ትኩረትም በቀጣይ ጊዜያት መሰል ጥያቄዎች ሊበረክቱ እንደሚችሉ ምልክት የሰጠ ሆኖ አልፏል።

👉 እየደመቀ የሚገኘው ዊሊያም ሰለሞን

ወጣቱ አማካይ ዊሊያም ሰለሞን ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በተለየ ብቃት ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ቡና አማካይ መስመር ከሁለቱ ስምንት ቁጥሮች አንዱ በመሆን የሚጫወተው ዊልያም በመከላከያ እና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ከግቦቹ ባለፈ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ዊልያም ሰለሞን ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ለአጥቂው አቡበከር ናስር ቀርቦ መጫወቱ ምናልባት ይበልጥ ግቦችን እንዲያስቆጥር የረዳው ይመስላል።

በተጨማሪም ከአማካዩ ሮቤል ተክለሚካኤል ጋር ጥሩ ጥምረትን እየፈጠረ የሚገኘው ዊልያም ኃላፊነት በተሞላበት ድፍረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በቀደሙት ጊዜያት በኳስ መቀበል እና ማቀበል ሂደቶቹ በጣም ለመጠንቀቅ ይሞክር የነበረው አማካዩ አሁን ላይ ግን በተሻለ ነፃነት ሲጫወት እየተመለከትነው እንገኛለን።

ከሜዳ ውጪ ባሉ ሁነቶች በአሉታዊነት ስሙ ከሰሞኑ ሲነሳ የነበረው አማካዩ አሁን ላይ ሜዳ ላይ እያሳየ በሚገኘው አስደናቂ ብቃት የተቺዎቹን አፍ እያዘጋ ይገኛል። ይህ ማለት ግን የሜዳ ውጪ ህይወቱን በስፖርታዊ ሥነምግባር ማስኬድ ካልቻለ የሰሞኑ ብቃቱ አብሮት ይቆያል ማለት አይደለም።

👉 ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ሜዳ ተመልሷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ከአምስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ዳግሞ ወደ ሜዳ ተመልሷል።

በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን አንድ ለምንም ከረቱበት ጨዋታ ወዲህ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ርቆ የሰነበተው ሱራፌል ዳኛቸው ቡድኑ ከባህር ዳር ጋር በነበረው ጨዋታ በተጠባባቂ ወንበር ላይ በመሆን ጨዋታውን ጀምሮ በመጨረሻ 30 ደቂቃዎች ተቀይሮ በመግባት መጫወት ችሏል።

በፋሲል ከነማ የማጥቃት ጨዋታ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሚናን የሚወጣዉ ሱራፌል ከጉዳት መመለሱ ለፋሲል ከነማ ከሚሰጠው ጥቅም ባለፈ የአፍሪካ ዋንጫው እየተቃረበ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ሚናን የሚወጣው ሱራፌል ወደ እንቅስቃሴ መመለሱ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተም እፎይታን የሚሰጥ ነው።

በቀጣይ የሚጠበቀው ነገር ሱራፌል በምን ያህል ፍጥነት የጨዋታ ዝግጁነቱን መልሶ ያገኛል የሚለው ጉዳይ ይሆናል።

👉 የመስፍን ታፈሰ ዕድገት ?

በሀገራችን እግርኳስ በርካታ አሳሳቢ ጉዳዮች ቢኖሩም ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው አንዱ እና አንገብጋቢው ጉዳይ ወጣት ተጫዋቾች በሚፈልገው መጠን ማደግ ያለመቻላቸው ጉዳይ ነው። በርካታ ተጫዋቾች የዚህ ሂደት ሰለባ ሲሆኑ መስፍን ታፈሰ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

በ2011 የውድድር ዘመን ከሀዋሳ ከተማ የዕድሜ እርከን ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ካደገበት ጊዜ አንስቶ በፍጥነት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን የበቃው መስፍን በተወሰነ መልኩ በራስ መተማመን ረገድ ካሳየው መሻሻል ውጪ በትልቁነቱ ሊነሳ የሚችል ዕድገት አሳይቷል ብሎ መነጋገር በጣም ከባድ ነው። እዚህ ወቅት ላይ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ጉዳይ አሁን ድረስ መስፍን ታፈሰ ከእምቅ ችሎታው አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ያህን ራሱን ወደ ትልቅ ተጫዋችነት በማሳደግ ረገድ ብዙ የሚቀሩት ጉዳዮች እንዳሉ ነው።

መስፍን ለግሩም አጥቂነት የሚበያበቁ አስደናቂ ፍጥነት ፣ ጉልበት እና ታታሪነትን የተላበሰ ቢሆንም አሁንም ከግብ ፊት ተረጋግቶ ውሳኔዎችን በመስጠት ረገድ በ2011 በነበረው መስፍንም ሆነ በአሁኑ መስፍን መካከል ይህ ነው የሚባል መሻሻሎች ለመመልከት አልቻልንም።

አሰልጣኞች ቡድኖችን ለጨዋታ ከማዘጋጀት ባለፈ በእጃቸው የሚገኙ ተጫዋቾች በማሻሻል ረገድ የሚጫወቱት ሚና የጎላ እንደሆነ ይታመናል። በዚህ መሰረት ግን አሰልጣኞች መስፍንን በግሉ የተሻለ ተጫዋች እንዲሆን በማድረግ ረገድ ሚናቸውን እየተወጡ አይገኝም ብለን መውቀስ ተገቢ ይመስላል። በተጨማሪም ተጫዋቹ በግሉ ራሱን ለማሻሻል ይበልጥ ተገቶ በመስራት ራሱን የበቃ ተጫዋቾች ለማድረግ መጣር ይኖርበታል።

👉 የተረሳው ጋብርኤል አህመድ

በ2003 የውድድር ዘመን በደደቢት መለያ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ተመልካች ትውውቅ ካደረገ ወዲህ በፕሪሚየር ሊጉ ከተመለከትናቸው ድንቅ የውጭ ሀገር ዜግነት ካላቸው አማካዮች አንዱ የነበረው ጋናዊው ጋብርኤል አህመድ አሁን ላይ ግን ስብስብ ከማሟላት ባለፈ በሜዳ ላይ ቡድኑን ሲያገለግል እየተመለከትን አንገኝም።

በደደቢት ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሀዋሳ ከተማ (በ2 አጋጣሚዎች) ፣ ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ ቆይታን ማድረግ የቻለው ተጫዋቹ ባለፉት ዓመታት ቀስ በቀስ ተፅዕኖው እየቀነሰ መጥቷል። በተለይም ከአምና ጀምሮ እጅግ ደካማ የሚባል ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል።

አምና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሀዋሳ ከተማ የተመለሰው ጋብርኤል ብዙ ተጠብቆበት ደቡብ ኢትዮጵያ ቢደርስም በተጠበቀው ልክ ቡድኑን ማገልገል አለመቻሉን ተከትሎ ቦታውን በወጣቱ ዳዊት ታደሰ ለመነጠቅ በቅቶ አመዛኙን የውድድር ዘመን በተጠባባቂነት ለማሳለፍ ተገዷል። ዘንድሮም በንፅፅር በጥራትም ሆነ በልምድ ያነሱ ተጫዋቾችን በያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ስብስብ ውስጥ እንኳን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጨዋታዎችን ለመጀመር እየተቸገረ ይገኛል።

የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ወደ ሊጋችን በሚመጡባቸው የመጀመሪያዎቹ የውድድር ዘመናት ድንቅ ብቃታቸውን ማሳየት ቢችሉም በሂደት ግን ፍፁም በሚያስደነግጥ ሁኔታ አቋማቸው መውረድ እየተለመደ መጥቷል። ከአቋማቸው መውረድ ጋር በርካታ ነገሮች በምክንያትነት ቢቀርቡም ጋብርኤል አህመድ ለዚህ ሂደት ምሳሌ የሆነ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል።

👉 ፍፁም ተፈሪ ዳግም በፕሪምየር ሊጉ

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን ለመጨረሻ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ የተመለከትነው ፍፁም ተፈሪ ዳግም በፕሪሚየር ሊጉ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሰበታ ከተማ መለያ ተመልክተነዋል።

የቀድሞው የደደቢት ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ንግድ ባንክ እና ሲዳማ ቡና አማካይ ፍፁም ተፈሪ በአምናው የውድድር ዘመን ክለብ አልባ ሆኖ ያሳለፈ ቢሆንም በክረምቱ የዝውውር መስኮት በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በተሰጠው የሙከራ ጊዜ በማሳመን ሰበታ ከተማን መቀላቀል ችሏል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስካሁን ለአዲሱ ቡድኑ ምንም ጨዋታ ሳያደርግ የቆየው ፍፁም ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 በረቱበት ጨዋታ በመጀመሪያ ተመራጭነት ተሰልፎ ለ45 ያክል ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል።

እርግጥ የመጀመሪያው ጨዋታ እንደመሆኑ ብዙም አመርቂ እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችልም በቀጣይ በፉክክር ጨዋታዎች የጨዋታ ደቂቃዎችን እያገኘ ሲመጣ የቀደመ ብቃቱን በሂደት መልሶ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የሲልቪያን ግቦሆ ስሜታዊነት

አይቮሪኮስታዊው አንጋፋ ግብ ጠባቂ ወልቂጤ ከተማን ከተቀላቀለ አንስቶ በጎ የሚባልን ተፅዕኖ ሜዳ ላይ ማሳረፍ የቻለ ቢሆንም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ስሜታዊነት የተሞላበት ተግባር በመፈፀም ብዙዎችን አሳዝኗል።

በ68ኛው ደቂቃ አካባቢ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ከመራችው እንስቷ አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ ውሳኔ ደስተኛ ያልነበረው ግብ ጠባቂው ከሊዲያ ጋር በፈጠረው አተካራ ቢጫ ካርድ ቢመለከትም በቢጫ ካርዱ ወቅት በነበሩ ቅፅበቶች በስሜታዊነት ከዳኛዋ ጋር ባደረገው ያልተገባ የቃላት ልውውጥ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ይህንን ብለዋል።

“ተገቢ አይደለም። ዳኛ የራሱ ውሳኔ ሊኖረው ይችላል ፤ እኔ ስለዳኛ መናገር አልፈልግም። እኛ እንደምንሳሳተው እነሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ። ስህተቱ ሲበዛ ነው መጥፎ። በአጠቃላይ እሱ የወጣበት ትልቅ ስህተት ነው። አንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ይህንን ማድረግ የለበትም ስለዚህ መታረም አለበት ብዬ እገምታለሁ። በዲስፕሊን ጉዳይ አልደራደርም።”

👉 “ብርቱካናማው ተራራ”- ውሀቡ አዳምስ

በ2013 የውድድር ዘመን እንደ ቡድን ፈታኝ የነበረን ጊዜን አሳልፈው በሁለተኛ ዕድል በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡት ወልቂጤ ከተማዎች በጣም ደካማ ለነበረው የተከላካይ መስመራቸው ፍቱን መድኃኒት ያገኙ ይመስላል። ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ወሀቡ አደምስ የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት እያሻሻለ ይገኛል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ወሀቡ አዳምስ ለወልቂጤ ከተማ መከላከል የነበረውን አበርክቶ በግልፅ የታየበት ነበር። ጨዋታውን ግሩም በሆነ የንቃት ደረጃ የከወነው ተጫዋቹ እርግጥ በተወሰነ አጋጣሚዎች ኃይልን በቀላቀለ መልኩ ቢሆንም የአትዮጵያ ቡናን ማጥቃት ቁልፍ የሆነውን አቡበከር ናስርን በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት እጅግ አስገራሚ ነበር።

በተጨማሪም ተጫዋቾቹ ያለው የቦታ ግንዛቤ እና ቦታ አያያዝ በጣም የሚያሰደንቅ ነበር። ግለሰባዊም ሆነ የወል የመከላከል ስህተቶች መገለጫው ለነበረው እና ዘንድሮ የመሻሻል እያሳየ ለሚገኘው የወልቂጤ የተከላካይ መስመር ወሀቡ አደምስ ሁነኛ መፍትሔ የሰጠ ይመስላል። ለዚህም ነበር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ በወጣበት ወቅት በሜዳ ላይ መቆየት አለበት በሚል ከቡድኑ ሀኪሞች ጋር የፈጠሩት አለመግባባት የተጫዋቹ ለቡድኑ ያለውን አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው።