ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ8ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት አሳይተዋል ያልናቸውን ተጫዋቾች እና ዋና አሰልጣኝ በማካተት ተከታዩን ምርጥ ቡድን አዘጋጅተናል።

አሰላለፍ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ፋሲል ገብረሚካኤል – ባህር ዳር ከተማ

ተመጣጣኝ አቋም ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች በታዩበት በስምንተኛው ሳምንት መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከወጡት መካከል ከበድ ያለ ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር የከወነው ፋሲል ገብረሚካኤልን ተመራጭ አድርገናል። ከፍ ያለ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ፋሲል የኦኪኪ አፎላቢን የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለት ከባባድ ሙከራዎች ባያድን ኖሮ የጨዋታው አጠቃላይ መልክ በተቀየረ ነበር።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወደ ቀኝ ባዘነበለው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ጥረት ውስጥ ታታሪው ሄኖክ እንደሁል ጊዜው በሜዳው ቁመት ወደ ፊት በመሄድ ተሳትፎ ሲያደርግ ታይቷል። ከምንም በላይ ግን ቡድኑን ሦስት ነጥብ ያስጨበጠችውን ጎል ሳይታሰብ ከረጅም ርቀት በመምታት በድንቅ ሁኔታ ማስቆጥሩ እና ጎሏ የጨዋታው ብቸኛ መሆኗ ክብደቷን ከፍ ስለሚያደርገው በቦታው ያለከልካይ እንዲመረጥ ምክንያት ሆኗል።

ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና

በጉዳት ከአሰላለፍ ርቆ የቆየው ጊትጋት በፋሲሉ ጨዋታ ጥቂት ደቂቃዎችን ተጫውቶ በ8ኛው ሳምንት በመጀመሪያ ተመራጭነት ወደ ሜዳ በተመለሰበት ጨዋታ የሲዳማን ዱካማ የመከላከል ሂደት በማሻሻል ድንቅ አቋም አሳይቷል። ሲዳማ ቡና አንድ ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ ጊትጋት ሰዓታቸውን በጠበቁ ሸርተቴዎች እና በግንባር ሦስት ወደ ግብነት ሊቀየሩ የተቃረቡ አጋጣሚዎችን በግል ብቃቱ አምክኗል።

ውሀብ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ

ምንም እንኳን ወልቂጤ እንደቡድን በሰራው የመከላከል ስህተት ከተጋጣሚው ሳጥን በተጀመረ የመልሶ ማጥቃት ግብ ተቆጥሮበት ይሸነፍ እንጂ የውሀብ አዳምስ አጠቃላይ ጥረት የሚደነቅ ነበር። ተጫዋቹ በከፍተኛ ትኩረት ጨዋታውን ሲያደርግ አቡበከር ናስርን የተቆጣጠረበት መንገድ እና በመጨረሻ ደቂቃ በተሰነዘረው የቡና ጥቃት ሦስት ተከታታይ ኳሶችን ከግብ መስመር ላይ ያዳነበት ቅፅበት ቡድኑ በሰፋ የግብ ልዩነት እንዳይሸነፍ ያደረጉ ነበሩ።

ሄኖክ አርፊጮ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሦስት የመሀል ተከላካዮችን በተጠቀመው የሀዲያ ሆሳዕና አሰላለፍ ውስጥ በግራ በኩል ያለውን የመሀል ተከላካይነት ቦታ የሸፈነው ሄኖክን በመስመር ተከላካይነት መርጠነዋል። በጨዋታው ከነበረው የመከላከል እና የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብ የማድረስ ጥሩ ሚና ባሻገር ፍፁም ቅጣት ምት በመሳቱ ሳይረበሽ ቡድኑን ለሁለተኛ ጊዜ አቻ ያደረገች እና ለድሉ መነሻ የሆነችውን ሌላ የፍፁም ቅጣት ምት በቁርጠኝነት በመምታት ማስቆጠሩ ተመራጭ አድርጎታል።

አማካዮች

ክሪዚስቶም ንታንቢ – ሰበታ ከተማ

ከተከላካዮች ፊት ባለው ቦታ ላይ የተለያዩ ጥምረቶችን እየሞከረ እስካሁን በዘለቀው የሰበታ ቡድን ውስጥ ዕድሉን ያገኘው ዩጋንዳዊው አማካይ ጥሩ የጨዋታ ዕለት አሳልፏል። ተጫዋቹ በቡድኑ ማጥቃት ውስጥ ኳስ በማሰራጨት ከነበረው ሚና በተጨማሪ እና በዋናነት ሰበታን ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ነጥብ ያስጨበጠች ብቸኛ ግብ በማስቆጠር የነበረው አስተዋፅኦ እንድንመርጠው አድርጎናል።

ሳምሶን ጥላሁን – ሀዲያ ሆሳዕና

በሊጉ ቡድኖች ውስጥ ያሉ የአጥቂ አማካዮች ተፅዕኖ ወረድ ብሎ በታየበት በዚህ ሳምንት የነብሮቹ አማካይ በንፅፅር የተሻለ በነበረው አፈፃፀሙ ልንመርጠው ችለናል። ታታሪው ሳምሶን እንደወትሮው ሜዳውን በማካለል የሆሳዕናን የማጥቃት እና የመከላከል ሽግግሮች ሲመራ የታየ ሲሆን ከተከላካይ ጀርባ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረሳቸው ኳሶችም ለቡድኑ ንፁህ የግብ ዕድልን የፈጠሩ ነበሩ።

ዊሊያም ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ውስጥ ያለው ኃላፊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገዘፈ የመጣው ዊሊያም በዚህም ሳምንት የነበረው ተፅዕኖ ዓይን የሚገባ ነበር። የቡድኑን የኳስ ፍሰት ከማሳለጥ ባለፈ ለአጥቂ መስመሩ ቀርቦ መንቀሳቀስ መቻሉ ለሙከራዎች ዝግጁ እንዲሆን እያደረገው ያለው ዊሊያም ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በእሱ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል። ግቧን በራሱ የግብ ክልል ከተጋጣሚ ባስጣለው ኳስ ረጅም ሜትሮችን ከአቡበከር ጋር በመናበብ እስከመረብ ያደረሰበት መንገድም የሚያስጨበጭብ ነበር።

አጥቂዎች

እንዳለ ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ

ጥሩ የቴክኒክ ብቃት ያለው እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሰብሮ መግባት ሲችል በቡድኑ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴም እየጎላ ሄዷል። ወደ ፍፁም ጥላሁን መስመር ያጋደለውን የቡድኑን የማጥቃት ሂደት በሚያመጣጥን መልኩ በዚህ ሳምንት በነበረው የሀዋሳው ጨዋታ በማጥቃቱ ላይ በነበረው ተሳትፎ የሪችሞንድ ኦዶንጎን ጎል በግሩም ሁኔታ ማመቻቸት ሲችል በመከላከሉ ላይ የነበረው ተሳትፎም በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከመስመር የሚነሳው ፈጣኑ አጥቂ አቤል ከግብ አስቆጠሪነት ይልቅ በተጋጣሚ የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መሀል አጥብቦ ወደ ሳጥን በመግባት የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ሲያግዝ ይታይል። በዚህ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለድል በበቃበት ጨዋታም በደካማ አጨራረስ ወደ ግብነት አይቀየሩ እንጂ ሁለት የመጨረሻ የግብ አጋጣሚዎች በዚሁ አግባብ በመፍጠር የበኩሉን መወጣት ችሏል።

ሀብታሙ ታደሰ – ሀዲያ ሆሳዕና

በሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ እና ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ከሌላው ቡድን ያልተናነሰ የነበረው ሀዲያ ግብ የማስቆጠር ችግሩን የሚቀርፍለት ሁነኛ ሰው ያገኘ ይመስላል። እንዳለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ ሀብታሙ አሁንም ለሀዲያ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። የመጨረሻ አጥቂነት ባህሪውን ባሳየባቸው አጨራረሶች ባስቆጠራቸው ግቦችም ለተከታታይ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል።

አሰልጣኝ

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ከአሸናፊነት ጋር ተራርቆ የቆየውን ሀዲያ ሆሳዕናን ለሁለተኛ ተከታታይ ድል ያበቁት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገን መርጠናል። በጨዋታው ሁለተኛ ሦስት ነጥብ ከማሳካት ባለፈ ቡድኑ ተፈትኖ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከመመራት በመነሳት ካስመዘገበው ድል ጀርባ የተረጋጋው የአሰልጣኙ የአመራር መንገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው።

ተጠባባቂዎች

አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር
መናፍ ዐወል – ባህር ዳር ከተማ
መሀሪ መና – ሲዳማ ቡና
እንየው ካሳሁን – ድሬዳዋ ከተማ
እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ
አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከተማ
ዳዋ ሆቴሳ – አዳማ ከተማ
ኤሪክ ካፓይቶ – አርባምንጭ ከተማ